ንጹህ ኢነርጂ አምራቿ ኢትዮጵያ በኮፕ-31 የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿን ለዓለም ታካፍላለች

You are currently viewing ንጹህ ኢነርጂ አምራቿ ኢትዮጵያ በኮፕ-31 የአረንጓዴ ልማት ስኬቶቿን ለዓለም ታካፍላለች

AMN- ጥቅምት 29/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከተፈጥሯዊ ውሃ፣ ንፋስ እና ጸሐይ የምታመነጨውን ታዳሽ ኃይል ለቀጣናዊ ልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ በማዋል ረገድ የያዘችውን ስትራቴጂያዊ ቁርጠኝነት በተግባራዊ እመርታዎች እያረጋገጠች ትገኛለች።

ሀገሪቱ ከምታመነጨው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚገኝ በመሆኑ በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አርአያነቷን ከፍ ባለ ደረጃ አጠናክራለች።

ይህ ስኬት ኢትዮጵያን በራሷ ብርሃን ከመብራት ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ማዕከል ወደመሆን አሸጋግሯታል።

የዚህ ታላቅ የታዳሽ ኃይል ስኬት መሠረት ከሀገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሲሆን በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል ዘመቻ የደንን ሽፋን ከማሳደጉ ባሻገር፣ ለአፈር መሸርሸርና ለደለል መከማቸት የሚዳርጉ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ይህ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች የተረጋጋ የውሃ ፍሰት እንዲኖራቸውና ለረጅም ዘመናት አቅማቸው ሳይቀንስ ኃይል እንዲያመነጩ አስተማማኝ መደላድል እንደሚፈጥር ይገለጻል።

ምንም እንኳን የውሃ ኃይል የሃገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዋና የጀርባ አጥንት ቢሆንም ከንፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች የሚገኘው ሀብትም የታዳሽ ኃይል ስብጥሩን የበለጠ አጠናክሮታል።

ኢትዮጵያ ከንጹህ ኃይል ብቻ እስከ 60 ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት ተፈጥሯዊ ጸጋ ያላት ሲሆን እ.ኤ.አ በ2030 የማመንጨት አቅሟን ወደ 15 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ አቅዳ እየሰራች እንደምትገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይህን ግዙፍ ሀብት ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት በማድረግ፣ የምታመርተውን ንጹህ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ በቀጣናው ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን ለማሳደግ ይረዳል።

በዚህ በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት ኢነርጂ አምራች ሃገራት ተርታ የምትሰለፈው እንዲሁም የኮፕ 32 አዘጋጅ የሆነቸው ኢትዮጵያ በነገው ዕለት በቱርክ አንታሊያ ከተማ በሚካሄደው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ላይ ትሳተፋለች።

በጉባኤውም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ ያስመዘገበቻቸውን ታላላቅ ስኬቶችና የአረንጓዴ ልማት ጥረቶቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታካፍል ይሆናል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review