AMN – ሕዳር 4/2019 ዓ.ም
አባይ ለኢትዮጵያውያን ውኃ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የአይበገሬነት ምልክት ነው።
የሀገሪቱ ህዝቦች ኪነ ጥበብን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ስለ አባይ ወንዝ ያላቸውን ቁጭት ለዘመናት ሲገልጹ ኖረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ በለገሰቻቸው የውኃ ሀብት፣ ለምለም አፈር እና ምቹ የአየር ጸባይ መጠቀም ተስኗቸው በድርቅ፣ በረሃብና በድህነት ሲሰቃዩ ቆይተዋል።
ከሀገሪቱ አልፎ ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም የሚተርፍ የውኃ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ፣ በባለጸግነቷ መጠቀም ሳይቻላት ቀርቶ ድህነትና ረሃብ መለያዋ እስከ መሆን ደርሷል።
በገዛ ሀገሩ ላይ በክብር መኖር፣ የዜጎቹን ህይወት መለወጥና ሀገሩን ማሳደግ ያልቻለው የአባይ ወንዝ ወደ ጎረቤት ሀገር ሲፈስ ግን ትልቅ ክብርና ደማቅ አቀባበል ሲደረግለት ቆይቷል።
ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመሰለ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ታታሪና ጠንካራ ህዝብ እያላት ለምን ተራበች? የሚለው ጥያቄ የበርካቶችን ምላሽ ይፈልጋል።
ግብጾች ከኢትዮጵያ በሚሄድላቸው ውኃ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግና የዜጎቻቸውን ኑሮ መቀየር ከቻሉ፣ ኢትዮጵያውያን አባይን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎችን ተጠቅመው ኢኮኖሚያቸውን ለምን ማሳደግ አቃታቸው? የሚለው ጉዳይም ተመሳሳይ ምላሽ የሚሻ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ፕሮጀክት ይህንን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ሀገራዊ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የሀገሪቱን ዜጎች የዘመናት ቁጭት ከመመለስና ቀጣናውን በሃይል ከማስተሳሰር አልፎ የሉዓላዊነትና የአይበገሬነት ምልክት ሆኗል።
አዲሱ ትውልድ ከመቆጨትና ከማዘን አልፎ ብሄራዊ ጥቅሙን በላቡ፣ በደሙ፣ በአንድነቱና በጽናቱ ማሳካት እንደሚችል ትልቅ ተምሳሌት ሆኗል።
ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስንና ጽናትን ያጎናጸፈው ፕሮጀክቱ፤ ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ቅኝ ግዛትን መዋጋት እና ሉዓላዊነትን ማስከበር እንደሚቻል በይፋ አረጋግጧል።
ግብጾች ለረጅም ዓመታት ሀሰተኛ ትርክቶችንና የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ በፈጠራ ሀብቷ እንዳትጠቀም የተለያዩ ሴራዎችን ቢፈጽሙም፣ ፕሮጀክቱ ኃይል እንዳያመነጭና ቀጣናውን በኃይል እንዳያስተሳሰር ማስቆም አልቻሉም።
ፈርዖኖቹ ኢትዮጵያን በግጭት፣ በእርስ በርስና በጦርነት አዙሪት ውስጥ ከትተው አባይን በብቸኝነት ለመጠቀም የተለያዩ ደባዎችን ለዘመናት ቢያካሄዱም፣ ኢትዮጵያን ማዳከምም ሆነ በልማቶቿ እንዳትጠቀም ማሰናከል አልቻሉም።
እንደ ህወሓት ያሉ ቅጥረኛ ሃይሎችም የግብጽን የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ኢትዮጵያውያንን በብሄርና በሃይማኖት ሽፋን ለማጋጨትና የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ለማስቆም ቢሯሯጡም፣ የህዝቦችን ህብረብሄራዊ አንድነት መርታት አልተቻላቸውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ መርሃ ግብር ላይ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ ያለፉት ዓመታት ሰንኮፉን ለመንቀል፣ አረሙን ለማረም፣ ዕንቅፋቱን ለማንሣት፣ መንገዱን ለመጥረግና መሠረቱን ለመጣል ከፍተኛ ትግል መደረጉን ማንሳታቸው፤ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ጸጋና ሀብቶቿን ወደ ተደራጀ ሀገራዊ አቅም ለመለወጥ ስታደርግ የነበረውን የጽናት ጉዞ የሚያሳይ ነው።

ዓለም ጀርባውን ሲያዞርብንና ፍርደ ገምድልነቱን ሲያሳየን፣ ለሴኮንድ ሸብረክ አላልንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ለማስከበር እና ግድባችንን ከፍጻሜ ለማድረስ ደፋ ቀና ስንል፣ በረጅም ገመድ አሥረው ሲጎትቱን ተንገዳገድን እንጂ አልወደቅንም ማለታቸው፤ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በበርካታ ፈተናዎች መካከል በጽናት መቆሟን የሚያረጋግጥ ነው።
በምግብና በወሳኝ ምርቶች ራሳችንን ለመቻል፣ በእግራችን ለመቆም የምናደርገውን መውተርተር ሲሳለቁበት አንገት ደፍተን አልቀረንም ሲሉ የተናጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ፤ የአይበገሬነታችንን መጠን ያወቅነው፣ ከመጽናት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን የተረዳንበት ጊዜ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ አድዋ ጀግኖች ጠንካራ የአይበገሬነት መንፈስን በመላበስ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅሞች ለማስከበር በጋራ መቆማቸው፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ብቸኛው አማራጭ ጽናት እና ህብረብሄራዊ አንድነት መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥ ነው።
በወንድማገኝ አሰፋ