AMN – ህዳር 5 /2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ከተማዋን አዲስ ገጽታን ከማላበስ አልፎ ፤ እንደ ስሟ ውብ አበባ፤ ለኑሮ ምቹ እና ለቱሪስቶችም ማራኪ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
ልማቱ መዲናዋን ከማሳመር እና ከማዘመን አልፎ የነዋሪዎቿንም የዕለት ከዕለት ኑሮ አዘምኗል፤ አዳዲስ የስራ ባህሎችንም ፈጥሯል፡፡
የህጻናት መጫወቻና የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የስፓርት ማዘዉተሪያዎች፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች፣ ዘመናዊ የህዝብ መጸዳጃ ስፍራዎች ተገንብተዋል፡፡
ግዙፍ ፓርኮች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያና ተርሚናሎች፣ ፋውንቴኖች ፣ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት፤ የመንገድ መብራቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ተረስተውና ተጥለው የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች፣ በልማቱ ተጠግነውና ተሻሽለው ለጎብኚዎች ክፍት ሆነዋል። አንድነት ፓርክና እንደ ታችኛው ቤተ መንግሥት ያሉት ታድሰውና ለነገው ዘመን ተዘጋጅተው ተጨማሪ ሀብት ማመንጨት ጀምረዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ዛሬ ላይ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ተዳርሷል፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ሌሎች ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች የከተሜነት ገጽታን መላበስ ጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምስረታ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ በልማቱ ከተማና ገጠሩ እኩል እየተቀየረ እና የከተሞችን ገመና ገላልጦ እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕይወት በሰቆቃ የሚገፋባቸው የመከራ ዳሶች፤ ንግድ፣ ሥራና አገልግሎት የማይሣለጥባቸው መተራመሻዎች፤ ፋይናንስ፣ ትራንስፖርት፣ ኔትዎርክ፣ መዝናኛና ታሪክ የማይተሣሠርባቸው መንደሮች እንደነበሩ የኮሪደር ልማት ገልጦ አሳይቶናል ነው ያሉት፡፡
በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞቻችን የዘመናዊ ከተማ መልክ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመኖሪያ የተመቹ፣ ለንግድና ለኮንፈረንስ የተስማሙ፣ ቢያስጎበኟቸው የማያሳፍሩ፣ ተምሳሌት ተደርገው የሚጠቀሱ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ “የአፍሪካ ውብ አበባ” ተብላ ብትጠራ፣ እውነታ እንጂ ባዶ ሙገሳ ተደርጎ አይወሰድም ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት የመጣንበት መንገድ እንደ ኮሪደር የተስተካከለ፣ እንደ ወንዝ ዳር ልማት ያማረ ብቻ አልነበረም፤ ብዙ ፈናዎችን ተሻግረናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ