አዲስ አበባን ተምሳሌት አድርጎ የተጀመረው አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ዛሬ ላይ በሁሉም የሃገሪቱ ማዕዘናት ተዳርሷል

You are currently viewing አዲስ አበባን ተምሳሌት አድርጎ የተጀመረው አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ዛሬ ላይ በሁሉም የሃገሪቱ ማዕዘናት ተዳርሷል

AMN- ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

በርካታ የዓለም ሃገራት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጡት ልዩ ትኩረት በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ወደ ኢኮኖሚያቸዉ ፈሰስ ያደርጋሉ፡፡

ቱሪዝም ከነዳጅና ከኬሚካሎች በመቀጠል፤ እንዲሁም ከምግብና ከአውቶሞቲቭ ምርቶች በመቅደም በዓለም ሶስተኛው ትልቁ የውጭ ንግድ ኢንዱስትሪ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

እንደ አሜሪካ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያሉ ሃገራት ከባህል፣ ታሪክና የባህር ዳርቻዎች፣ ከመዝናኛና ከታወቁ ብሔራዊ ፓርኮች፣ ከከተሞችና ከንግድ ቱሪዝም ፣ ከታሪካዊ ህንጻዎች እና የምግብ ባህል፣ ከሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች እና ሰው ሰራሽ ደሴቶች፣ ከዘመናዊነትና ቅንጦት ከተሞላበት ሕይወት ከፍተኛ የቱሪዝም ገቢ እንደሚያገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

እነዚህ ሃገራት ከዘርፉ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ መሆን የቻሉበት ዋናው ምስጢር ለቱሪዝም ዘርፍ ከሚሰጡት ትኩረት በተጨማሪ ምቹ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እና ጠንካራ የሃገር ገጽታ በመገንባታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ሰፊ የባህልና የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሯቸውም ለቱሪዝም ዕድገት ምቹ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ባለመገንባታቸው ከቱሪዝም ዘርፍ በሚገባቸው ልክ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻሉም፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ በታሪክ፤ በባህልና በተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች ሃገር ብትሆንም ያሏት የቱሪዝም ሃብቶች ለዘመናት አቧራ ለብሰው ከመዝለቃቸውም በላይ ይህ ነው የሚባል ገቢ ለሃገሪቱ ማስገኘት አልቻሉም፡፡

ከለውጡ ወዲህ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተባባሪነት እና በመደመር እሳቤ ከቱሪዝም ማዕድ ለመጋራት በተደረጉ ብርቱ ጥረቶች በርካታ የቱሪዝም ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት አዲስ አበባን ተምሳሌት አድርጎ የተጀመረው የአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚሉ ተነሳሽነቶች በሁሉም የሃገሪቱ ማዕዘናት ተዳርሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቱሪዝም መዳረሻ ልማት መስክ እየተሰሩ ካሉ በርካታ ስራዎች ጎን ለጎን ቱሪስቶች መዳረሻዎቹን እንዲጎበኙ የማስተዋወቅ ስራም በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review