AMN – ታኀሣሥ 7/2017 ዓ.ም
በቀድሞው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተቋቋመው “የአዳም ፋውንዴሽን” ይፋ ሆነ።
በሸራተን አዲስ በተከናወነው የማብሰሪያ መርሐ ግብር የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የአዳም ፋውንዴሽን ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመተባበር የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ በማድረግ በአፍሪካ መቀንጨርን የማስቆም ዓላማ አንግቧል።
ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በቁጥር 7260/24 የተመዘገበ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
ቁርጠኝነት፣ ማብቃት፣ ትብብር፣ ፈጠራ፣ ልህቀት፣ አካታችነት እና በህፃናት ላይ ማተኮር የአዳም ፋውንዴሽን መሰረታዊ እሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
የአዳም ፋውንዴሽን መሥራች እና የቦርድ ሊቀ መንበር የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ በመሪነት ዘመኔ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የተመጣጠነ ምግብ መሆኑን ተረድቻለሁ።
የአዳም ፋውንዴሽን ግብርና፣ትምህርት፣ ማህበራዊ ጥበቃ፣ ምግብ ማቀነባበር፣ ጤናና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል በፕሮጀክቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደመቀ፤ አፍሪካ አጀንዳ 2063 ግቡን እንዲመታ ለማገዝ ፋውንዴሽኑን ለመመስረት አነሳስቶኛል ብለዋል።
በዚህም የቀጣዩን ዘመኔን የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን በማስፋት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ብልጽግና የበኩሌን ለመወጣት በቁርጠኝነት እሰራለሁ ብለዋል።
አምራችና የበቃ የሰው ሀይል ለመፍጠር በቅድሚያ ሥርዓተ ምግብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በአካላዊ እና አዕምሯዊ ጤናው የዳበረ ትውልድ ለማፍራት የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ውስጣዊ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ሥርዓተ ምግብ የግለሰቦች ሳይሆን ዓለም አቀፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፥ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትን መገንባት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።



All reactions:
73You, Us Man Mohammed and 71 others