AMN – ጥር 21/2018 ዓ.ም
መንግሥት የሀገሪቱን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ሰፊ ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ገለፁ።
ሚኒስትር ዴኤታው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ከማስገባት ባለፈ፣ ነባርና ዕድሜ ጠገብ የሆኑ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የመቀየር ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ተሽከርካሪ ወደ ሀገር በማስገባት የተሰማሩ አስመጪ ነጋዴዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኢሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሽያጭ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነዳጅ ተሽከርካሪ በማስመጣትና በመገጣጠም ይሰሩ የነበሩ ተቋማት ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሰሩ እየተደረገ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ቀደም ሲል ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የጥራት ክፍተቶችን ለመቅረፍም፣ የሀገሪቱን የመልክዓ ምድርና የአየር ንብረት ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡ ጥብቅ መመዘኛዎች በመዘርጋት ላይ ናቸው።
በመዲናዋ የሚገኙ የመኪና አስመጪዎችና ሻጮች እንደሚሉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግብይት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።
ቀደም ሲል ተጠቃሚዎች በቴክኖሎጂው ላይ የነበራቸው ጥርጣሬና ዝቅተኛ ፍላጎት ተቀይሮ፣ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መላመድና እንደ ዋነኛ ምርጫቸው መውሰድ ጀምረዋል ብለዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ከነዳጅ መኪናዎች ጋር ሲነጻጸሩ ያላቸው ተመጣጣኝ ዋጋ፣ አስተማማኝነትና እጅግ አነስተኛ የሆነው የጥገና ወጪ አሁን ላይ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም የአረንጓዴ ትራንስፖርት ጽንሰ ሀሳብ በህዝቡ ዘንድ እየሰረጸ መምጣቱ ብዙዎች ወደዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሳቡ እያደረጋቸው ይገኛል።
በበረከት ጌታቸው