AMN- ሚያዚያ 6/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አማካኝነት የነገውን ዓለም ዛሬ ለመቀላቀል በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ለውጥ ውስጥ ያላትን ሚና አስመልክቶ ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለጻቸውም ሀገሪቱ “ዘግይቶ መድረስ” ከሚያስከትለው ጣጣ ወጥታ፣ የነገውን ዓለም ቀድሞ በመረዳት የፈጠራ ምንዳን መቋደስ እንዳለባት አስገንዝበዋል።
በመረጃ ትንተና እና በፈጠራ ሥራ፣ ከትንሽ ጅማሮ በመነሳት ዛሬ ላይ ከፍተኛ ሀብት ማፍራት የቻሉ ኩባንያዎችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ፣ በሶላር ሴል ማምረት እና በኤሮስፔስ ዘርፍ የቦይንግ መለዋወጫዎችን ለማምረት ፋብሪካዎችን እያጠናቀቀች እንደምትገኝም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ያለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ይህም በኢንዱስትሪ 4.0 ውስጥ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
ዓለም አቀፋዊ የንግድ ፉክክር፣ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እና ያልታሰቡ ወረርሽኞች በሎጂስቲክስና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ ለመቋቋም ንቁ መሆን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በታምራት ቢሻው