የተከታታይነት እጦት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ስብራት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የተከታታይነት እጦት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ስብራት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚታየው የተከታታይነት እጦት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ስብራት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ አዲሱን የኢንዱስትሪ መስፋፋት ዘመን እየተቀላቀለች ያለችበትን ሂደትና የመንግስትን አቅጣጫ አብራርተዋል።

ቀደምት መንግስታት የሰሩትን ተተኪው ትውልድ የማፍረስ ልማድ ለኢኮኖሚው መቀጨጭ ትልቅ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ለማስተካከል ካለፈው ስህተትና ስኬት የመማር እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

መንግስት ካለፈው ታሪክ ጠቃሚ ስራዎች እንዲቀጥሉ ብዝሃ ዘርፍ፣ ብዝሃ ተዋንያን እና ብዝሃ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ አዲስ እሳቤ ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

መንግስት ቀጥታ አስፈጻሚ ከመሆን ወጥቶ፣ ለኢኮኖሚው ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥርና የሚያመቻች ሚና እንዲኖረው መደረጉን ጠቁመዋል።

ለኢኮኖሚው እድገት እንቅፋት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የውጭ ኢንቨስተሮች እንዳይመጡና የሀገር ውስጥ ምርታማነት እንዲቀንስ ማድረጉንም አስረድተዋል።

ቀደም ሲል በብድር የተገነቡ ፋብሪካዎች ብድራቸውን እንኳ መመለስ የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ግንባታዎች የትና መቼ ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ? የሚለውን ጥናት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ለይስሙላ በየቦታው ፋብሪካዎችን አቁሞ ውጤት አልባ ከመሆን ይልቅ፣ ውጤት የሚያስገኙትን በጥራት ሰርቶ ማጠናቀቅና ማሳደግ የመንግስት ዋነኛ ስትራቴጂ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review