AMN – ሚያዝያ 9/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል፣ የምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እና የኑሮ ዘይቤን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት ቴክኒካል አማካሪ አቶ ዋለልኝ ዳሳለኝ ገለጹ፡፡
አማካሪው አቶ ዋለልኝ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በከተማዋ የሚገኙ ወንዞች መበከል በአየርና በውሃ አማካኝነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤ ሆነው ቆይተዋል።
በተለይም በወቅቶች መለዋወጥ ምክንያት የሚፈጠረው መጥፎ ሽታ ለመተንፈሻ አካል ጤና ትልቅ ተግዳሮት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን የተከናወነው የወንዞች ዳርቻ ልማት እነዚህን ተላላፊ በሽታዎች በዘላቂነት ለማስቀረት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ልማቱ ከአካላዊ ጤንነት ባለፈ ለነዋሪዎች ሥነ-ልቦናዊና አዕምሯዊ ደኅንነት ያለውን ጠቀሜታ ያብራሩት አቶ ዋለልኝ፤ ፕሮጀክቶቹ ሕፃናት የተሟላ ዕድገት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ አስተማማኝ የመጫወቻ ሜዳዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተገቢውን ዕረፍት የሚያገኙባቸው አረንጓዴ ስፍራዎች እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ምቹ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች መካተታቸው ለጤናማ አኗኗር የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የምግብ ደኅንነትን ከማረጋገጥ አኳያም የወንዞቹ መጽዳት በመዲናዋ ዙሪያ የሚከናወኑ የከተማ ግብርና ውጤቶች ላይ የሚታየውን የብክለት ስጋት እንዲቀንስ ማድረጉን አቶ ዋለልኝ አውስተዋል።
በዚህም በወንዝ ዳርቻ የሚመረቱ የጓሮ አትክልቶችና የወተት ተዋጽኦዎች ከብክለት የጸዳ ውሃ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ማኅበረሰቡ ጤናማ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ አስችሏል።

ወንዞቹ ከቆሻሻ በመጽዳታቸው ውሃው ለሁለተኛ ዙር አገልግሎት እንደሚውል የገለጹት አቶ ዋለልኝ፤ ይህም ለከተማ ዉበት ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪና ለከተማ ግብርና የሚውል የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ትልቅ ግብዓት መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ነዋሪዎች ከመኪና ጋጋታ ነፃ በሆነና ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የከተማዋን የኑሮ ሁኔታ ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት እያሸጋገረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው