የድልድዮቹ ድርብ ፋይዳ

You are currently viewing የድልድዮቹ ድርብ ፋይዳ

ድልድዮች ሰዎችን የሚያስተምሩ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሆነው ከተሰሩ ለከተሞች መታወቂያ ወይም መለያ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል

በከተሞች ምስረታ፣ መስፋፋት እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቁልፍ ሚና ካላቸው መሰረተ ልማቶች መካከል ድልድይ አንዱ ነው። የድልድይ ዋና ተግባር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሸጋገሪያ ሆኖ ማገልገል ቢሆንም ምልክታዊ (Symbolic)፣ ታሪካዊና ባህላዊ ትርጉም አለው። ከምልክታዊነት አኳያ የጎልደን ጌት ድልድይ ሁሌም ከአሜሪካዋ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳል። ከታሪካዊ ትርጉም አንጻር፣ ድልድይ በተገነባበት ወቅት የነበረው ምርጥ ቴክኖሎጂ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በደቡባዊ ፈረንሳይ ኒምስ አቅራቢያ የሚገኘው እና የሮማውያንን የላቀ ቴክኖሎጂ የሚያሳየው ፖንት ዱ ጋርድ እና ሌሎችን መጥቀስ እንደሚቻል “Values of Bridges in the Formation of Cities” በሚል ርዕስ በደቡብ ኮሪያ የሲቪል ምህንድስና ባለሙያዎች የወጣው ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁለንተናዊ መልክ ገፅታዋ እየተቀየረ መጥቷል። የመዲናዋ ምልክት፣ ውብ ገፅታ ማሳያ፣ የአይን ማረፊያና የቱሪስት መስህብ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል ደግሞ ድልድዮች ይጠቀሳሉ። በከተማዋ ከተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ጋር ተያይዞ ወፍራምና ጥንካሬ ያላቸው የመስታወት ንጣፎችን በመጠቀም ማራኪ፣ የዘመኑ የምህንድስና ውጤት ማሳያ የሆኑ የእግረኛ የመስታወት ድልድዮች በተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ድልድዮቹ ለነዋሪዎች ከመሸጋገሪያነት ባለፈ ብዙ ትርጉም አላቸው።

ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ መሸጋገሪያ ከሆነው ታሪካዊ የራስ መኮንን ድልድይ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የእግረኛ መሸጋገሪያ የመስታወት ድልድይ ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በዓድዋ ድል ጀግናው ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ስም የሚጠራው ድልድዩ፣ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ ከላይ በጋሻ ታጥሮ፤ የእግረኛው መተላለፊያ ደግሞ መስታወት ሆኖ ወደ ታች ከርቀት ያለውን ውሃ በሚያሳይ መልኩ ተገንብቷል። በአሁኑ ወቅት ከእግረኛ መተላለፊያነት ባሻገር የከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች በአግራሞት የሚመለከቱት፣ ብዙዎችም ፎቶ የሚነሱበት ሆኗል።

አቶ አክሊሉ አሰፋ በኔዘርላንድ አምስተርዳም ከተማ ነዋሪ ናቸው። ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ መጥተው በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ የመስታወት ድልድዩ ላይ ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው ፎቶ ሲነሱ ነበር ያገኘናቸው። የራስ መኮንን ድልድይን ከዓመታት በፊት እንደሚያውቁትና አዲስ የተሰራውን የመስታወት ድልድይ ለማየት መምጣታቸውን ይናገራሉ። “ውሃው ቆሻሻና ሽታ ነበረው። አሁን ንጹህ ሆኖ ነው የሚታየው። የእግረኛ መተላለፊያ መንገዱ መስታወት ሆኖ ከላይ ወደ ታች ሲታይ በጣም ያምራል፡፡ ድልድዩ ሰዎች ጥሩ ነገሮችን የሚያዩበት፣ የሚዝናኑበት እንዲሁም ለቱሪስት መስህብ የሆነ ስፍራ ሆኗል” ይላሉ።

ወይዘሮ ትዝታ ደምሴ ከአራት ኪሎ የእግረኛ የመስታወት ድልድዩን በማቋረጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር ያገኘናቸው። “ተወልጄ ያደኩት ስድስት ኪሎ ስለሆነ አካባቢውን አውቀዋለሁ። ለዓይን ማራኪና ምቹ አልነበረም፤ አይደለም ሊዝናኑበት ይቅርና በአካባቢው ሲታለፍ ወደ አፍንጫ የሚመጣው ከወንዙ የሚወጣ ጠረን መጥፎ ነበር። አሁን አካባቢው በጣም ውብና ምቹ ሆኗል። በእርግጥ በመስታወት ድልድዩ ለመሻገር የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ ጓደኛዬ በዚህ ለመሻገር ስለምትፈራ በውጭ በኩል ባለው መንገድ ነው የምትሄደው። ከመሻገሪያነቱ ባለፈ እንዝናናበታለን፤ ፎቶ እንነሳበታለን፤ ደስ ነው የሚለው” ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት አጋርተውናል።

እስጢፋኖስ አካባቢም ልዩ የምህንድስና ጥበብ የሚታይበት የሚያምር የመስታወት ድልድይ ይገኛል። አቶ ማሞ ገበየሁ ትውልድና እድገታቸው አራት ኪሎ አካባቢ ነው። የእግረኛ የመስታወት ድልድዩ ለአካባቢው ልዩ ውበትና ገፅታን ያላበሰ መሆኑን፣ “ከዚህ ቀደም አስታውሳለሁ፤ እስጢፋኖስ ድልድይ ያለበት አካባቢ እንደአሁኑ ግልጥ ያለ አልነበረም፡፡ ግራና ቀኝ የነበረው አካባቢ ዳዋ የዋጠውና ቆሻሻ ነበር። አሁን በጣም የሚያምርና ደስ የሚል፤ ሰዎች ለማስታወሻ ፎቶ የሚነሱበት ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ቢያልፈው ስንሻውም በእስጢፋኖስ አካባቢ ባለው የእግረኛ መተላለፊያ የመስታወት ድልድይ ሲሻገሩ ነበር ያገኘናቸው። “የስራ ቦታዬ ካዛንቺስ ስለሆነ ስመላለስ የበፊቱ ድልድይና አካባቢው ምን እንደሚመስል አውቀዋለሁ። ከድልድዩ በታች የነበረው አካባቢ አረምን ጨምሮ በተለያዩ ነገሮች የተዋጠ፣ ቆሻሻ ነገሮች የሚታዩበት፣ የእግረኛ መተላለፊያ ድልድዩም በጣም ጠባብ ነበር። አሁን ሰፊና የሚያምር የእግረኛ ድልድይ ተገንብቷል፤ በጣም ደስ ይላል። መስታወት መሆኑ ትንሽ ያስፈራል፤ ግን ለዓይን ያምራል፡፡ ሰው በእግሩ እንደልብ እየተንቀሳቀሰ ይዝናናበታል” ብለዋል።

የእስጢፋኖስ አካባቢ በወንዝ ዳርቻ ልማት ውብ ገፅታን ተላብሶ ተገንብቷል። “የአዲስ አበባ ወንዞች ትንሳኤ” በሚል ርዕስ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተላለፈው ጥናታዊ ፊልም ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ እንደተናገሩት፣ “በሁሉም ቦታዎች ነባር ድልድዮች ተጨማሪ ለከተማዋ ገፅታ ሊያላብሱ የሚችሉ፣ የማንነት መገለጫና ምልክት በሚሆን መልኩ ታድሰዋል።” በእስጢፋኖስ ድልድይ ላይም ቀድሞ ሲል የነበረው የእግረኛ መንገድ ወደ ተሽከርካሪ መንገድ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ለከተማዋ ያማረ ገፅታ የሚያላብስ ለእግረኛ አዲስ የመስታወት ድልድይ ተገንብቷል። ድልድዩ እግረኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል። ከድልድዩ ስርም የሳይክልና የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች ተሰርተዋል።

እስጢፋኖስ አካባቢ ባለው የእግረኛ መተላለፊያ የመስታወት ድልድይ ከላይ በቀለበት ቅርፅ ብረቶች በሚያምር መልኩ ተቀምጠው ይታያሉ። ይህም “በሰላም እለፉ፤ ሰላም ይሁን” የሚል ትርጉም አለው። በድልድዩ ሲሻገሩ በመስታወት ወደ ታች ውሃውን እየተመለከቱ መሻገር የሚያምር ሁኔታን ይፈጥራል። ድልድዩ ጥበባዊ መልክን መላበሱን፣ ለቱሪስቶች የሚነገር ታሪክ እንዲይዝ ተደርጎ ውብ በሆነ መልኩ መገንባቱን የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ድልድይ ሲገነባ የመሬት አቀማመጥ፣ ወንዝና ሸለቆ ያለበት መሆኑ ለገፅታ ወሳኝነት አለው። ዋናው ዓላማውም መንደርን ከመንደር፤ አካባቢን ከአካባቢ፣ ማዕከላትን ከማዕከላት ጋር ማገናኘት ነው። በአዲስ አበባ አፍንጮ በርን፣ ፒያሳን፣ ቀበናን፣ ኡራኤልን እና ባምቢስን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ድልድዮች ተገንብተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ከመሸጋገሪያነት ባሻገር ኪነ ጥበባዊ ውበትን የተላበሱ፣ ዘመኑን የሚመጥኑ፣ በተለያየ ዲዛይን የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድ ያካተቱ ድልድዮች እየተገነቡ ነው። በአፍንጮ በር፣ እስጢፋኖስ፣ ፒያሳና አራት ኪሎ አካባቢ የተገነቡ ድልድዮች ለዚህ ማሳያ ናቸው። የከተማዋን ውበትና መልካም ገፅታ አጉልተዋል፤ ከፍ አድርገዋል። ከድልድይነት አገልግሎታቸው ባሻገር ሰዎች ድልድዩን ሲሻገሩ ቀልብ የሚስቡ ነገሮችን ይመለከታሉ። ይህም ቱሪስቶችን ይስባል። ለምሳሌ፡- በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘው ጎልደን ጌት ድልድይ በዓለም ላይ ከሚጎበኙ ውብ ድልድዮች አንዱ ነው። በተለያዩ የዓለም ከተሞችም ተአምራዊ የሆኑ ድልድዮች እንደሚገኙ ዳንኤል (ዶ/ር) ያነሳሉ።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል ሆነው የተሰሩት ዘመናዊ የመስታወት ድልድዮች የከተማዋን ውበትና ገፅታ ከፍ እንዳደረጉ የሚያነሱት ዳንኤል (ዶ/ር)፤ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር ድልድዮች ላይ በግራና ቀኝ ውበትን የሚያስጠብቁ፣ የኢትዮጵያን ባህልና ትውፊትን የሚገልፁ ነገሮችን በመጨመር መስራት ያስፈልጋል። ድልድዮች ወንዞች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚሰሩ እንደመሆናቸው ልሙጥ ሳይሆን ሰዎችን የሚያስተምሩ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሆነው ከተሰሩ ለከተሞች መታወቂያ ወይም መለያ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ በቻይና በመስታወት የተሰሩ በርካታ ድልድዮች ይገኛሉ። ታዋቂው የዣንግጂያጂ ግራንድ ካንየን ድልድይ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንደኛው መሆኑን አብራርተዋል።

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review