ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን የባህሪ ግንባታ ክበብን የተመለከተ ነው፡፡ እናንተ ትሳተፋላችሁ? ተሳትፎ ማድረጋችሁስ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራችሁ ምን ያህል አግዟችኋል? ከጎደኞቻችሁ ጋር ሀሳብ ተለዋወጡ። ያነጋገርናቸው የመሀል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆች የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
በረከት አሻግሬ እባላለሁ፡፡ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ ከዚህ በፊት አስተማሪ ሲያስተምር ከጎን ካሉት ጓደኞቼ ጋር አወራ ነበር። ሌሎችን የማክበር ልምዴ አናሳ ነበር፡፡ የመታዘዝም ችግር ነበረብኝ። በባህሪ ግንባታ ክበብ መሳተፍ ከጀመርኩ በኋላ ግን መጥፎ ሥነ ምግባር መሆኑን በመረዳት አስተካክያለሁ። በአሁኑ ወቅት አስተማሪ ሲያስተምር አላወራም፤ አልረብሽም። ማንኛውንም ሰው አከብራለሁ፤ እታዘዛለሁ። እንደ ታማኝነት፣ ቅንነት የመሳሰሉትን የሥነ ምግባር እሴቶች በደንብ እንዳውቃቸው አድርጎኛል። ጥሩ ሥነ ምግባር ኖሮኝ ማደጌ በወደፊት ህይወቴ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ሂክማ ከበደ እባላለሁ፡፡ 11 ዓመቴ ሲሆን የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። በክበቡ ውስጥ መሳተፍ የጀመርኩት ከሦስተኛ ክፍል ጀምሬ ነው። ይህንን ክበብ ወድጄው ነው የምሳተፈው፡፡ ክበቡ በተማሪዎች ሥነ-ምግባርና ውጤት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡ ወደ ክበቡ ከመቀላቀሌ በፊት ረባሽ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በዚህም ትምህርቴን በአግባቡ ስለማልከታተል የትምህርት ደረጃዬ ከ11ኛ እስከ 20ኛ ባለው ውስጥ ነበር፡፡
ክበቡ ውስጥ ስመዘገብ በመጀመሪያ ስለ ትምህርት ጥቅም፣ መረበሽ ስለሚያመጣው ጉዳትና ስለ እውቀት ሰፊ ምክሮች ተሰጥተውኛል። በዚህም መሠረት መረበሽ ሙሉ በሙሉ አቁሜያለሁ፡፡ መምህራን ሲያስተምሩ በሥነ ስርዓት እከታተላለሁ፡፡ የሚሰጠኝን የክፍልና የቤት ሥራ ተግባራት በአግባቡ እሰራለሁ፡፡ ሥነ ምግባሬን በማሻሻል አሁን ጎበዝ ተማሪ መሆን ችያለሁ፡፡ መምህራን ለእኛ ምን ያህል እንደሚለፉና ምክራቸውን መስማት ለወደፊት ሕይወት ስኬት መሠረት እንደሆነ ተረድቻለሁ። ጥሩ ሥነ ምግባሬ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አስገኝቶልኛል፡፡
ናሆም ዳግማዊ እባላለሁ፡፡ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ እድሜዬም 13 ነው። በባህሪ ግንባታ ክበብ ውስጥ መሳተፍ የጀመርኩት በዚህ ዓመት ነው። ቀደም ሲል በክፍል ውስጥ ወሬ በማውራት አስተማሪዎችንና ተማሪዎችን በመረበሽ እታወቅ ነበር፡፡ በክበቡ መሳተፍ መቻሌ መረበሼን ትቼ በትምህርቴ ላይ ትኩረት እንዳደርግ አስችሎኛል። ለመምህራንና ለቤተሰቦቼ አክብሮቴና ታዛዥነቴ ጨምሯል፡፡ በሰዎች ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፎልኛል፡፡ ለወደፊት ሕይወቴም ሥራን በታማኝነት ለመስራት ያግዘኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሳምራዊት ሽፈራው እባላለሁ። የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። ለእኔ ሥነ ምግባር ማለት አንድ ሰው ሊኖረው የሚችለው ፀባይ ነው። እሱም ጥሩ እና መጥፎ ሥነ ምግባር ተብሎ በሁለት ይከፈላል። ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በክበቡ እየተሳተፍኩ እገኛለሁ፡፡ እንዴት ጥሩ ውጤት እንደምናመጣ፣ አንድ ጥሩ ተማሪ ሊኖረው ስለሚገባው ባህሪ ዙሪያ እንወያያለን፡፡ በዚህም መረበሽ፣ ትምህርት አለመከታተል የመሳሰሉት ሥነ ምግባሮች የሉኝም፡፡ በክበቡ መሳተፌ መምህራኖቼ የሚሰጡኝን ምክር በመጠቀም ታናናሾቼን እንድመክር ረድቶኛል።
ልጆች መምህር ጌታሁን አርዓያ እባላለሁ፤ በትምህርት ቤት የግብረ ገብ መምህር እና የባህሪ ግንባታ ክበብ ሰብሳቢ ነኝ፡፡ ልጆች የባህሪ ግንባታ ክበብ መሳተፋችሁ ጥሩ ሥነ ምግባር እንድታዳብሩ፣ የመምራት፣ የማስተባበር እና በሰዎች ፊት የመናገር ብቃታችሁን እንድታሳድጉ ይረዳችኋል። ትምህርታችሁን በሥርዓት እንድትከታተሉና ውጤታማ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፡፡ ለመምህራኖቻችሁና ቤተሰቦቻችሁ ታዛዥ እንዲሁም ቅን እንድትሆኑም ያግዛችኋል፡፡
አያችሁ ልጆች መልካም ባህሪ ወይም ሥነ ምግባር ተላብሳችሁ ማደጋችሁ በትምህርታችሁ ጎበዝ፣ ወደፊት በምትሰሩት ሥራ ውጤታማ ትሆናላችሁ፤ በሕግና ሥርዓት እንድትመሩ ይጠቅማችኋል፡፡ በራስ መተማመናችሁ እንዲጨምር፣ መብታችሁን እንድትጠቀሙና ግዴታችሁን እንድትወጡም ያግዛችኋል።
ልጆች በአጠቃላይ በባህሪ ግንባታ ክበብ መሳተፋችሁ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በሥነ-ምግባር የታነፃችሁ፣ ለራሳችሁና ለሀገራችሁ የሚጠቅም መልካም ዜጋ ሆናችሁ እንድታድጉ ይረዳችኋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ