በሚያዝያ ወር ውስጥ አዲስ አበባ ሶስት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶችን ታስተናግዳለች
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ድንቅ ታሪኳ የዓለምን መድረክ በወርቅ ስሟን ስታስጠራ ብትኖርም፣ የዓለምን ኮከቦች በገዛ ምድሯ አስተናግዳ የፉክክር ሜዳ ስትሆን ማየት የብዙዎች የዘመናት ናፍቆት ነበር። ለዓመታት በዓለም አቀፍ የሩጫ መድረኮች የድል አርማ ሆና የዘለቀችው ኢትዮጵያ፣ አሁን ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ኮከቦች የሚሰባሰቡባት መዳረሻ መሆን ችላለች። የኢትዮጵያ ስም ከድል ጋር በተቆራኘበት በዚሁ አትሌቲክስ፣ የዓለምን ምርጥ ስፖርተኞች በአዲስ አበባ ምድር ላይ ተገኝተው ከኢትዮጵያውን አትሌቶች ጋር ሲፎካከሩ ማየት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አቀፍ የአንድ ቀን ውድድር (Addis Ababa Grand Prix One Day MeetingContinental Tour) አዘጋጅ ሆና በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር መካተቷ፣ የሀገሪቱን ስፖርታዊ ልዕልና ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። ይህ መድረክ ጀግኖች አትሌቶችን በደጋፊዎቻቸው ፊት ከዓለም ምርጦች ጋር ትከሻ ለትከሻ የሚለኩበት ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ቱሪዝም ካርታ ላይ በደመቀ ቀለም የሚያሰፍር ትልቅ አጋጣሚ ነው።
በዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) የውድድር መርሃ-ግብር መሰረት፣ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ የምታስተናግደው ታሪካዊው የ“አንድ ቀን ውድድር” የዓለምን ዓይን ወደ ኢትዮጵያ የሚያዞሩና ታላላቅ ኮከቦችን የሚሰበስብ እንደሚሆን ይጠበቃል። በተለይም በከፍታ ቦታ (High Altitude) ላይ የሚደረግ ውድድር መሆኑ፣ ለርቀትና ለመካከለኛ ርቀት ሯጮች ትርጉም ከፍ ያለ ነው።
በዚህ ውድድር ላይ በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር የታወቁና ስመ-ጥር የሆኑ ከ70 በላይ የዓለም እና የሀገር ውስጥ ኮከቦችን በአንድ መድረክ ያገናኛል። በተለይም በዳይመንድ ሊግና በጎልደን ስፓይክ መድረኮች ስማቸው ገዝፎ የሚነሳ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ኢየን ቼፕቴጌይ ወይም ጃኮብ ኪፕሊሞ ያሉ የኬንያውያንና የኡጋንዳውያን ዝነኛ የርቀት ሯጮች በኢትዮጵያ ምድር ከኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጋር ሲፋለሙ ማየት ለስፖርቱ አፍቃሪ ትልቅ ድግስ ነው።
በዚህ ታሪካዊ ውድድር ላይ በዋናነት የሚጠበቁት የአፍሪካ የ100 ሜትር የሪከርድ ባለቤት ፈርዲናንድ ኦማንያላ፣ የኦሎምፒክ የ200 ሜትር ሻምፒዮኗ ጋቢ ቶማስ እና የ2019 የዓለም ሻምፒዮኗ ዳሊላ መሐመድ ናቸው። እነዚህ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ቁንጮዎች ከአዲስ አበባው ደማቅ ደጋፊ ጋር የሚገናኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ እንደ ጉዳፍ ፀጋይ እና ዳዊት ሥዩም ያሉ የዓለም ድል አድራጊዎችና በርካታ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባለቤቶች የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ምንም እንኳ አዲስ አበባ በርቀት ሩጫ ብትታወቅም፣ በከፍታ ቦታ ላይ የሚደረጉ የ100 እና የ200 ሜትር ውድድሮች ለአጭር ርቀት ሯጮች የሰዓት ማሻሻያ (Speed boost) ስለሚሰጡ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የሚመጡ ፈጣን አትሌቶች አዲስ ታሪክ ለመስራት ወደ አዲስ አበባ ሊያቀኑ ይችላሉ።
ይህ መድረክ እንደ ለሜቻ ግርማ፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ታምራት ቶላ ያሉ የዓለም የሪከርድ ባለቤቶችና የኦሎምፒክ አሸናፊዎች በገዛ ሀገራቸው ህዝብ ፊት ብቃታቸውን የሚያሳዩበት ልዩ አጋጣሚ ነው። ከውድድሩ ጎን ለጎንም እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ያሉ የአትሌቲክስ ስመ-ጥሮች በክብር እንግድነት ተገኝተው ለውድድሩ ዓለም አቀፋዊ ድምቀት እንደሚሰጡት ይታመናል።
የዓለም አትሌቲክስ አዲስ አበባን የመረጠው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ ከተማዋ ያላትን የ‘አትሌቶች መፍለቂያ’ ስም እና አሁን ላይ እያደገ የመጣውን የስፖርት መሠረተ-ልማት ታሳቢ በማድረግ ነው። በሌላም በኩል አትሌቶች ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺህ 355 ሜትር ከፍታ ላይ መወዳደራቸው ሳንባቸውንና ጽናታቸውን ለመፈተሽ ትልቅ ዕድል ይሰጣል ተብሎለታል። እንደዚሁም በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ አትሌቲክስን የሚወድና የሚረዳ ደጋፊ በመሆኑ፣ ስታዲየሙን የሚሞላው ደማቅ ድባብ ለቴሌቪዥን ስርጭትና ለስፖርቱ ማርኬቲንግ ከፍተኛ ዋጋ አለው።
አዲስ አበባ ይህንን ታላቅ የዓለም አቀፍ ውድድር እንድታስተናግድ ከተመረጠችባቸው ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያስመዘገበችው አስደናቂ የመሠረተ-ልማት ለውጥ ነው። ከተማዋን ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎቿ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ ሰፋፊ መንገዶችና የእግረኛ መሄጃዎች አዲስ አበባን ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ገጽታ አላብሰዋታል። ይህም ለውድድሩ የሚመጡ አትሌቶችና እንግዶች ያለምንም እንግልት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
መዲናዋ የዓለም አቀፍ የአንድ ቀን ውድድር አዘጋጅ እንድትሆን ያስቻላት ሌላኛው ምክንያት በስፖርታዊ መሠረተ-ልማት ረገድ ያስመዘገበችው አስደናቂ እድገት ነው። ከተማዋ ያሏት ታሪካዊ ስታዲየሞች በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ዘመናዊ የሩጫ ትራኮች እንዲገጠምላቸውና የመወዳደሪያ ቁሳቁሶቻቸው እንዲሟሉ መደረጉ፣ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እምነት እንዲያተርፉ አድርጓቸዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዳይሬክተር ፒርስ ኦካላጋን በበኩላቸው ውድድሩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲስ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል። ዓለም የኢትዮጵያን አትሌቶች በሚገባ ያውቃቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ መጠቀም ለቀጣዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ መሠረት የሚጥል እንደሆነ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም “ከሥድስት ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ አልነበረውም፤ በዚህ ፍጥነት ትራኩ ተሰርቶ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱ ተዓምር ነው” ብለዋል።
ከዋና ዋና ስታዲየሞች በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የተገነቡት የስልጠና ማዕከላትና ፕሮጀክቶች አትሌቶች ከውድድር በፊት ብቃታቸውን የሚያሟሉባቸው ዘመናዊ የጂምናዚየም፣ የሕክምና እና የማገገሚያ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችለዋል። በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለስፖርቱ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ፣ የተመልካቾች መቀመጫዎች፣ የቪ.አይ.ፒ ማረፊያዎችና የጋዜጠኞች የሥራ ክፍሎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው መገንባታቸው አዲስ አበባን ለቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትና ለታላላቅ እንግዶች አቀባበል ምቹ አድርጓታል። ይህ የመሠረተ-ልማት ሽግግር፣ ኢትዮጵያ ስፖርታዊ ኩነቶችን በማዘጋጀት ረገድ ያላትን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ምሰሶ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) አንድን ከተማ ለአዘጋጅነት ከመምረጡ በፊት የሚመለከተው፣ “ስታዲየሙ የት ነው?” የሚለውን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የከተማዋን ዝግጁነት ጭምር ነው። እንደዚሁም ከዋናው ስታዲየም ጎን ለጎን የተገነቡት የመለማመጃ ሜዳዎች አትሌቶች ያለምንም እንግልት ለውድድር እንዲዘጋጁ ስለሚረዱ ለምርጫው ትልቅ ክብደት ሰጥተውታል።
የዓለም አትሌቲክስ የውድድሮች ዳይሬክተር ፒርስ ኦካላጋን በአዲስ አበባ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት፣ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የማሟላትና ታላላቅ ውድድሮችን በብቃት የማደራጀት አቅም እንዳላት መስክረዋል። የዓለም አትሌቲክስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፣ “ኢትዮጵያ ለዓለም አትሌቲክስ እድገት ያበረከተችው አስተዋጽኦ ወደር የለውም። አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ የውድድር ካላንደር ውስጥ መካተቷም፣ ስፖርቱን በዓለም ዙሪያ ተደራሽ ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ስኬት ነው” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ዕድል በማግኘቷ “የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የስፖርት ዲፕሎማሲ እና የስፖርት መሰረተ ልማት መስፋፋት ስራችን ፍሬ እያፈራ ይገኛል” ሲሉ ገልፀዋል። ይህ አጋጣሚ ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ለዓለም የምታሳይበት መሆኑን የገለጹት፣ ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚንስትሯ ሸዊት ሻንካ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ፣ ፌዴሬሽኑ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር የጀመረውን የስፖርት ዲፕሎማሲ ወደ ከፍታ በማድረስ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት በማስቻል አዲስ ምዕራፍ አስመዝግቧል ብሏል። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ የውድድሩን ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የጠበቀ ዝግጅት ስለመደረጉም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ መገኛ ከመሆኗም በተጨማሪ አዳዲስና ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የሚለው ደግሞ የስፖርት ባለሙያው ይድነቃቸው ግርማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለዝግጅ ክፍላችን ሀሳቡን ያጋራው በመዲናዋ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝ የሆነው ይድነቃቸው እንደሚለው፣ ይህ ውድድር ኢትዮጵያ ከአትሌት አምራችነት ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ክስተቶችን በብቃት መምራት የምትችል ‘ተደማጭ ስፖርታዊ ኃይል’ መሆኗን የምታስመሰክርበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው።
የዓለም አትሌቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ውድድሩ እንደ ዓለም ሻምፒዮና ወይም ኦሎምፒክ በአንድ ወቅት ተከብሮ የሚያልቅ ሳይሆን፣ በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች የሚዘዋወር የሊግ ውድድር አካል ነው። በውድድሩ ላይ በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉበትና በሰዓትና በነጥብ የሚፎካከሩበት መድረክ ነው። ውድድሩ በዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ በመሆኑ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ዘንድ ይደርሳል።
ዛሬ (ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም) ከሚካሄደው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን የአትሌቲክስ ውድድር በተጨማሪ በዚህ ወር ውስጥ ሁለት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህም ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር እና ግራንድ ኢትዮጵያን ራን ናቸው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ