AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርን (Addis Ababa Grand Prix) ትላንት በታላቅ ድምቀት አስተናግዳለች።
ውድድሩ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ታላላቅ ስፖርታዊ መድረኮችን የማዘጋጀት ከፍተኛ ብቃትና አቅም እንዳላት በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።
በስፍራው ተገኝቶ ውድድሩን የታዘበው ናይጄሪያዊው የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ ጆን እንደገለጸው፤ በአዲስ አበባ የታየው ዝግጅት በቻይና፣ በሮም ወይም በማንኛውም የዓለም ክፍል ከሚካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ጋር እኩል የሚመጥን ነው ሲል አሞካሽቶታል ፡፡
ይህም አፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች በአህጉሪቱ የማስተናገድ ፍላጎትና አቅም እንዳላት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ ደማቅ ዝግጅት በትውልድ ሃገሩ በናይጄሪያ ዋሪ ከተማ እንዲካሄድ ያለውን ምኞት ገልጿል።
ለዝግጅቱ ስኬት የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፤ ውድድሩ በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑም ተመላክቷል።
በበረከት ጌታቸው