ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ህዋ ጥርጊያ መንገድ እመቤት ሙሀባው ማን ናት?

You are currently viewing ከኢትዮጵያ ምድር ወደ ህዋ ጥርጊያ መንገድ እመቤት ሙሀባው ማን ናት?

AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም

እመቤት ሙሀባው የኤሮስፔስ ዘርፍ ተመራማሪ እና የጠፈር ትውልድ አማካሪ ምክር ቤት (Space Generation Advisory Council) የአፍሪካ ቀጣና አስተባባሪ ናት፡፡

በዘርፉ ያላትን ጥልቅ እውቀትና ልምድ በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ በጠፈር ምርምር ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ በቁርጠኝነት የምትሰራ ባለሙያ ናት፡፡አሁን ደግሞ በ2029 ወደ ህዋ ለመምጠቅ በመጠባበቅ ላይ የምትገኝ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ዕጩ ጠፈርተኛ በመሆን ታሪክ ለመስራት ተቃርባለች፡፡

የዓለም ሴቶች “ይቻላል” የታሪካዊ ጉዞ ማሳያ
የእመቤት ሙሀባው ጉዞ የግል ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያውያንና ለዓለም ሴቶች የ”ይቻላል” መንፈስ ህያው ምስክር ነው፡፡ የጠፈር ምርምር ለተመረጡ ጥቂት ሀገራት ወይም ወንዶች ብቻ የተተወ አለመሆኑን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

ሴቶች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በሒሳብ (STEM) ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ በሆነበት ዓለም፣ እመቤት “ጠፈር ሩቅ አይደለም” በማለት ለወጣቶች አዲስ ራዕይ ሰጥታለች፡፡

ይህ ንግግሯ ልክ እንደ ቫለንቲና ቴሬሽኮቫ (የመጀመሪያዋ ሴት ጠፈርተኛ) ሁሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች ወደ ሰማይ ቀና ብለው ትልቅ ህልም እንዲያልሙ በር ይከፍታል፡፡

በኤ.ኤል.ኤክስ (ALX) ኢትዮጵያ እና በኢዲዛ የፈጠራ ስቱዲዮ በተዘጋጀው የዩሪ ጋጋሪን መታሰቢያ ላይ እንዳለችው፣ ወጣቶች ተሰጥዖቸውን ከፍላጎታቸው ጋር ማጣመር አለባቸው ፡፡

እሷ የኤሮስፔስ ኢንጂነር የመሆን ህልም ያላቸውን ለማገዝ ቃል መግባቷ፣ ለተተኪው ትውልድ መሰላል የመሆን ትልቅ የሴትነት ጥንካሬ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በጠፈር ምርምርና ምህንድስና ያላት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት የምታሳስበው እመቤት፣ በ2029 የምታደርገው በረራ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጠፈር ካርታ ላይ በጉልህ እንድትሰፍር ያደርጋታል፡፡

የእመቤት ሙሀባው ወደ ህዋ የማቅናት ህልም፣ የቴክኖሎጂ ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች ብርታት፣ ለሀገር ኩራት፣ ለሴቶች ደግሞ የድል አርማ ነው። 2029 የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በህዋ ላይ በሴት ጠፈርተኛ እጅ የሚውለበለብበት ታሪካዊ ዓመት ለመሆን ጥቂት ዓመታት ብቻ ቀርተውታል፡፡

“ጠፈር ሩቅ አይደለም፤ ህልማችሁን ሰማይ ላይ ስቀሉት!” የሚለው መልዕክቷ ዛሬም በብዙዎች ልብ ውስጥ እያስተጋባ ይገኛል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review