አዲስ አበባ ከአፍሪካ ኩራትነት ወደ ዓለም አቀፍ የከተማ ልማት ተምሳሌትነት ተቀይራለች- የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ተሳታፊዎች

You are currently viewing አዲስ አበባ ከአፍሪካ ኩራትነት ወደ ዓለም አቀፍ የከተማ ልማት ተምሳሌትነት ተቀይራለች- የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ተሳታፊዎች

AMN- ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በተካሄደው የ2026 የግራንድ ፕሪክስ ውድድር ተሳታፊ የሆኑ ስመጥር የትራክ ኮከቦችና ዓለም አቀፍ እንግዶች፣ በከተማዋ እየታየ ባለው ፈጣን ለውጥና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እጅግ መደመማቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጓትንና ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነች መሆኑን የውድድሩ ተሳታፊና ጎብኚዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከተማዋን የጎበኙ የተለያዩ አትሌቶች በሰጡት አስተያየት፣ አዲስ አበባ እጅግ በጣም ውብ፣ ንፁህና የተደራጀች ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።

በተለይም በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች መዲናዋን ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር እኩል ተወዳዳሪ እያደረጓት መሆኑን በቆይታቸው መታዘባቸውን ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ አክለውም በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም ሕፃናትንና ሁሉንም የዕድሜ ክልሎች ያማከሉ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ለስፖርቱ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል፤ አትሌቶች በሁሉ ነገር እንዲበረቱ የሚያደርጉና የጀግና አትሌቶችን ታሪክ የሚዘክሩ የስፖርት ፓርኮች መገንባታቸው ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

ከመሠረተ ልማቱ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዶችን በቅንነትና በፍቅር የመቀበል ባህሉ ጎብኚዎች በቤተሰብ መካከል እንዳሉ ሆኖ እንዲሰማቸው ማድረጉን አንስተዋል።

ከተማዋ ያላት ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ጣፋጭ ምግቦችና ቆንጆ መስተንግዶ ለመዲናዋ የቱሪስት መስህብነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጎብኚዎቹ አንስተዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም፣ ኢትዮጵያ በታሪክ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ አሁን ላይ በልማትም የአፍሪካ ኩራት እየሆነች መሆኑን በአካል መመልከታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን እየገነባች እንደምትገኝና እዚህ ያለው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለሌሎች ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎቹ ምስክራቸውን ሰጥተዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review