ኢትዮጵያን እና ፈረንሳይ ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋገጡ

You are currently viewing ኢትዮጵያን እና ፈረንሳይ ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋገጡ

AMN ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ከሚገኘዉ ከፀደይ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከፈረንሳይ ግምጃ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ከፍተኛ ደረጃ ያለው ውይይት አካሂደዋል።

ውይይቱም የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያለውን ስልታዊ አስፈላጊነት ዳግም ያረጋገጠ ነበር።

ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የልማት ትብብር ማጠናከር፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ቅንጅትን ማሳደግ እና በኢትዮጵያ አጠቃላይ የዕዳ ሽግሽግ ላይ ያለውን ጠንካራ እንቅስቃሴ ማስቀጠል በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን የሪፎርም ፕሮግራም እና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመደገፍ በአለም ባንክ እና በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በኩል የጠበቀ ትብብር ስለማድረግ ተወያይተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ፈረንሳይ ለምታሳየው ወጥ እና ገንቢ ተሳትፎ አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ሀገሪቱ በይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ውስጥ ተባባሪ ሊቀመንበር በመሆን ለምትጫወተው ግንባር ቀደም አመራር ትኩረት ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ ፈረንሳይ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር የተሳካ የሁለትዮሽ ስምምነት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ረገድ ያላትን ቁልፍ ሚና ገልጸዋል።

እንዲሁም የዕዳ ዘላቂነትን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና አዳዲስ የፋይናንስ ፍሰቶችን ለማስገኘት ወሳኝ በሆነው ከግል አበዳሪዎች ጋር በሚደረገው ቀጣይ ድርድር ፈረንሳይ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጉልተዋል።

ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ ለመደገፍ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማምጣት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸዉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review