የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው – ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

You are currently viewing የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር ነው – ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

AMN – ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ ጋር ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ኅብረት መካከል ያለውን ዘመናት የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አስተማማኝ አጋር መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ኅብረቱ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኃይል ልማት በመደገፍ እያበረከተ ለሚገኘው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም የአውሮፓ ኅብረት ኢንቨስትመንቶች የኢትዮጵያን የልማት ዕድሎች በመጠቀም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የጋራ ተጠቃሚነት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል አስተማማኝና ተዓማኒነት ያለው ወዳጅነት የጋራ ዕድገትን በሚያስቀጥል መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ተገማችና ዕምነት የሚጣልበት ወዳጅነቶችን ለማጎልበት በቁርጠኝነት የምትሰራ ሀገር መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት እየገነቡ ከሚገኙ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካና ለአጠቃላይ አህጉሪቱ መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ኅብረቱ የኢትዮጵያን የብልፅግና ግስጋሴ በመደገፍ የልማት አጋርነቱን እያስቀጠለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በገጠር የኃይል ልማት ተደራሽነት ላይም ኅብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በቀጣይም ኅብረቱ ለኢትዮጵያ ልማት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኑን አረጋግጠው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት መፂኢ ዕድል ለአውሮፓ አስፈላጊ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነትን በማስቀጠል የጋራ ጥቅምና ዘላቂ ወዳጅነት ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review