AMN ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራቶች ብቻ በርካታ ዲፕሎማቶችን በመቀበል የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂካዊ ማዕከልነቷን በተግባር አረጋግጣለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከቡሩንዲ፣ከላይቤሪያ እና ከፖርቹጋል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በአዲስ አበባ ስኬታማ ውይይት አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የብራዚል፣ የቱርክ፣ የማሌዥያ፣ ጣሊያን እና የእስራኤል መሪዎችን እንዲሁም የቻይና እና የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ተቀብለው አነጋግረዋል።
እንደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ታንዛኒያ ያሉ ከዘጠኝ በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም በሁለንተናዊ አጋርነት ዙሪያ በአዲስ አበባ መክረዋል። በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ጎን ለጎን የተከናወኑ ከ15 በላይ የሁለትዮሽ ውይይቶችም የሀገሪቱን ቀጠናዊ መሪነት ዳግም አድሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሀገር ውጭ በብሪክስ (BRICS) ጉባኤ ላይ እንደ ሙሉ አባል ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖ አረጋግጠዋል። በቤጂንግ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም፣ በአዘርባጃን COP29 እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተደረጉ ጉብኝቶችም ለሀገሪቱ ተሰሚነት አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
ይህም በጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ከተከናወኑ የሰላም ጥረቶች እንዲሁም ከዓለም ባንክ እና IMF ጋር ከተደረጉ ታሪካዊ ስምምነቶች ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የድርድር አቅም ወደ ላቀ ከፍታ አሸጋግሮታል። በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ኅብረት የአለምአቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲከላ ጋር ተገናኝተው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስላለው የረጅም ጊዜ ትብብር ውይይት ማድረጋቸዉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡