ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል

You are currently viewing ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል

AMN ሚያዝያ 25/ 2018 ዓ.ም

በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ የተለየ ትኩረት ከሚያገኙ ጨዋታዎች መካከል ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል የሚያደርጉት አንዱ ነው፡፡ በጋራ 40 የሊግ ዋንጫዎችን ያሸነፉት የእንግሊዝ ሃያላን ክለቦች የዘንድሮ አላማቸው በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን የሚያስገኝ ደረጃን መያዝ ነው፡፡

ሁለቱም ክለቦች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ተቃርበዋል፡፡ ካከናወናቸው 34 ጨዋታዎች 61 ነጥቦችን የሰበሰበው ዩናይትድ ታሪካዊ ተቀናቃኙን ማሸነፍ አልያም አቻ መለያየት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎውን ያረጋግጥለታል፡፡

የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ58 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ ዛሬ ድል ከቀናው በሂሳባዊ ስሌት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎውና ባያረጋግጥም በእጅጉ ይቃረባል፡፡

ማንችስተር ዩናይትድ ከአስደንጋጩ የሊድስ ዩናይትድ ሽንፈት በኋላ ቼልሲ እና ብሬንትፎርድን በመርታት አገግሟል፡፡ ክለቡን በጊዜያዊነት እየመራ የሚገኘው ማይክል ካሪክም ቡድኑን በቋሚነት ለመምራት ብቃቱ እንዳለው ፍንጭ እየሰጠ ይገኛል፡፡

እንግሊዛዊው አሰልጣኝ በተጫዋችነት ዘመኑ በስኬት ያሳለፈበትን ክለብ በ13 ጨዋታዎች መርቶ ዘጠኙን በድል ሲወጣ ፣ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቶ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡ ማግኘት ከሚገባው 39 ነጥብ 29ኙን አሳክቷል፡፡ ካሪክ ዩናይትድን ከተረከበ በኋላ ይህን ያህል ነጥብ የሰበሰበ ክለብ የለም፡፡

ሊቨርፑልም ሰሞነኛ አቋሙ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የአርነ ስሎቱ ቡድን የመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎችን በድል ተወጥቷል፡፡ እነዚህ ድሎች የተሸለ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

በዛሬው ወሳኝ ጨዋታ ሞሐመድ ሳላህን በጉዳት ማጣቱ ግን አሳሳቢ ይሆናል፡፡ ግብፃዊው ተጫዋች ምንም እንኳን ዘንድሮ ምርጥ ብቃቱ ላይ ባይገኝም ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ያለው ክብረወሰን አስደናቂ ነው፡፡

የ33 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች በኦልድትራፎርድ ባደረጋቸው ስምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ወይ ግብ አስቆጥሯል ፤ ወይ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡ በአጠቃላይ 13 ግቦችን ዩናይትድ መረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባቱን ያስመዘገበው ኦልድትራፎርድ ላይ እንደሆነ የኦፕታ ቁጥራዊ መረጃ ያሳያል፡፡

ዩናይትድ በበኩሉ አምበሉ ቡርኖ ፈርናንዴዝ ላይ ጥገኛ ይመስላል፡፡ የግብ ዕድል በመፍጠር በሊጉ አቻ የማይገኝለት አማካዩ ታሪክ ለመስራት ተቃርቧል፡፡ ፖርቹጋላዊው ተጫዋች በውድድር ዓመቱ 19 ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችን አቀብሏል፡፡ በሊጉ ታሪክ ክብረወሰኑን የያዙት ቴሪ ኦንሪ እና ኬቨን ቀብሩይና 20 ኳሶችን አመቻችተዋል፡፡ ቡርኖ ይህን ታሪክ ለመጋራት ወይም የግሉ ለማድረግ የዛሬን ጨምሮ አራት ጨዋታዎች ይቀሩታል፡፡

በዛሬው ጨዋታ ዩናይትድ ማቴኡስ ኩኝሃን መልሶ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቅጣት ላይ የሚገኘው ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ግን አይኖርም፡፡ በሊቨርፑል በኩል ከሞሐመድ ሳላህ ውጪ ሁጎ ኢኪቲኬ ለጨዋታው አይደርስም፡፡ አሌክሳንደር ኢዛክም አዲስ ጉዳት እንደገጠመው እየተነገረ ይገኛል። ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ግን ወደ ልምምድ ተመልሷል፡፡

ሊቨርፑል በቅርብ ዓመታት በዋነኛ ተቀናቃኙ ላይ ያለው የበላይነት እየጎላ መጥቷል፡፡ ቀዮቹ ከዩናይትድ ጋር ባደረጓቸው 19 የመጨረሻ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸው በሦስቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአንፊልድ 2ለ1 የተረቱበት ይጠቀሳል፡፡ ሊቨርፑል በኦልድትራፎርድም ቢሆን ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከመጨረሻዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፏል፡፡

ዳረን ኢንግላንድ በዋና ዳኝነት የሚመሩት ጨዋታ ዛሬ 11፡30 ሲል በኦልድትራፎርድ ይከናወናል፡፡

በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች 10 ሰዓት ላይ ቦርንማውዝ ከ ክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ምሽት 3 ሰዓት አስቶንቪላ ከ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ይፋለማሉ፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review