ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማስጀመራቸውን ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማስጀመራቸውን ገለጹ

AMN- ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም

ዛሬ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነውን የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጀምረውልናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በከተማችን ብሎም በሀገራችን ለዘመናት የአገልግሎት ዘርፉን ለመለወጥ ሳይቻል ስር በሰደደ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተተብትቦ የኖረ ቢሆንም መንግስት ቃል በገባው መሰረት ችግሩን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የሚለውጥ ‘የመሶብ’ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር ለተገልጋዩ እፎይታን ይዞ መጥቷል ብለዋል።

ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈፀም ተከታታይነት ያለው የማያቋርጥ ተግባር እያከናወን ነዉ በማለትም ገልጸዋል።

ከቴክኖሎጂ ዝግጅት አንፃር ወጪን የሚቆጥብ (በየማዕከላቱ የዳታ ማዕከል ግንባታን የሚያስቀር)፣ የአገልግሎት ጥራት እና ወጥነትን የሚያረጋግጥ፣ በሁሉም ማዕከላት ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የUnified Infrastructure Model ተግባራዊ ማድረግ መቻላችን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነዉ ሲሉም አክለዋል።

የተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የአዲስ መሶብ አገልግሎትን በተሟላ ደረጃ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ ህዝባችን ባለበት ቦታ ሆኖ አገልግሎት እንዲያገኝ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በአውቶቡሱ ላይ የአገልግሎት መስጫ ሥራ፣ የሀይል አማራጭ ሥራ (ከፀሓይ ብርሃን)፣ ፈጣን የኔትወርክ አማራጭን (MPLS = Multi Protocol Label Switching) በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ተደርጓል፣ የካሜራ ገጠማ እና የኮንፊግሬሽን ሥራ ተጠናቋል፣ የአገልግሎት መስጫ መሠረታዊ ግብዓቶች ተሟልቶ፣ የሙከራ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ ተደርጓል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት የተጀመሩ አገልግሎቶች፦

– የገቢ አገልግሎት (አዲስ ቲን ማውጣት)

– የንግድ አገልግሎት (ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ)

– የጤና (ለመንጃ ፈቃድ አካላዊ የጤና ምርመራ)

– የሲቪል ምዝገባ (የመታወቂያ ዕድሳት እና ልደት)

– የአሸከረካሪ ተሽከርካሪ (የመንጃ ፈቃድ እና የቦሎ ዕድሳት)

– የኢትዮ ፖስታ (የመንገድ ፈንድ ክፍያ)

– የብሔራዊ መታወቂያ (አዲስ ምዝገባና የመረጃ እርማት)

– የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ቅድመ ክፍያ)

የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው

ዛሬ ባስጀመርነው የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ህዝብ ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መሄድ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ራሱ ወደ ህዝቡ እንዲጠጋ የማድረግ እድልን ይፈጥራል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review