አድማስ ተሻጋሪው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት

You are currently viewing አድማስ ተሻጋሪው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት

AMN- ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

በእነዚህ ለውጦች ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሪነት ሚና ተጠቃሽ ነው። ይህ ብርቱ ትጋታቸውም በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎችን ለኢትዮጵያና ለአመራራቸው አስገኝቷል።

በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ወይም ሻምፒዮን አድጎ ሾሟቸዋል።

ሹመቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች የምትገኘውን የላቀ ሚና እውቅና ለመስጠት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነትና ለውጤታማ አመራራቸውም የተሰጠ ዕውቅና በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃና በቱሪዝም ዘርፍ የታዩ ስኬቶች ሀገሪቱን በዓለም መድረክ በአዲስ መልክ እንድትታወቅ ያደረጉ ናቸው።

ይህ የአመራር ሚናቸው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ተችሮታል። ኢትዮጵያ ለብዙ አሥርት ዓመታት ስንዴን ከውጭ በማስገባት የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ሰትፍጨረጨር ነው የቆየችው።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ አዲስ የመሪነት አቅጣጫ ተከትለዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሉ አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲደራጁና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ከፍተኛ ማነቃቀትን ፈጥረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የስንዴ ፍላጎቷን በራሷ እንድትሸፍንና ወደ ጎረቤት ሀገራት መላክ እንድትጀምር ያደረጋትን ስኬት አምጥቷል።

በስንዴ ልማት የተገኘው ድንቅ ስኬት በዓለም አቀፉ የግብርና እና የምግብ ድርጅት (ፋኦ) ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነው። እ.ኤ.አ በ2024 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና ረገድ ላሳዩት ቁርጠኝነት የአግሪኮላ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የአረንጓዴ ዓሻራ መርሐ-ግብርን በተከታታይ ዓመታት በመፈጸም ታሪክ ሠርታለች።

በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን በእጽዋት የማልበስ ዘመቻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ የሚመራ ሲሆን፣ በአንድ ጀምበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተመዘገበው የዓለም ክብረ ወሰን፣ ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር ያላቸውን የአመራር ብቃት የሚያረጋግጥ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ኢትዮጵያን በአካባቢ ጥበቃ ረገድ የአፍሪካ ድምፅ እንድትሆን አድርጓታል። በተባበሩት መንግሥታትና በተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ድርጅቶች ዘንድም የላቀ የአፍሪካ መሪነት ዕውቅና እንዲሰጣቸው አስችሏል።

በፈረነረጆቹ ታኅሣሥ 2022 በዋሺንግተን የሚገኘው የአሜሪካ አካዳሚ ኦፍ አቺቭመንት ኤንድ ግሎባል ሆፕ ኮሊሽን የላቀ አፍሪካዊ አመራር ዕውቅናን በአረንጓዴ አሻራ ላስመዘገቡት ውጤት አበርክቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጡት ትኩረት ሀገርን በሁሉም ዘርፍ መገንባት የሚለውን መርሃቸውን ያንጸባርቃል። እንደ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ያሉ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የተፈጥሮና የታሪክ ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ቀይረዋል።

በመዲናዋ አዲስ አበባ የተገነቡት እንደ አንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች፣ እንዲሁም በክልሎች የተገነቡት የኮይሻ፣ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ ሸበሌ እና ደንዲ የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃሳብ አፍላቂነትና ክትትል የተከናወኑ ናቸው።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትም የከተሞችን ገጽታ በመቀየር የቱሪስቶችን ፍሰት ከፍ አድርጓል። የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ የዕውቅና ሽልማት የሰጠ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2019 የዓለም ቱሪዝም ፎረም “የቱሪዝም መሪ” በሚል የክብር ሰርተፊኬትን፣ ቱሪዝም ለማስፋፋት ለሰጡት አመራራር ዕውቅና አበርክቶላቸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በቱሪዝም ልማት እና በዲጂታላይዜሽንና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም አዲስ ተስፋ የፈነጠቁ ናቸው።

ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎቹ ለአመራር ብቃታቸው ምስክር ከመሆናቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ተጨማሪ የሞራል ጉልበት ይሆናሉ።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review