ዶናልድ ትራምፕን ኢላማ አድርጎ ተኩስ የከፈተዉ ተጠርጣሪ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባል

You are currently viewing ዶናልድ ትራምፕን ኢላማ አድርጎ ተኩስ የከፈተዉ ተጠርጣሪ ነገ ፍርድ ቤት ይቀርባል

AMN-ሚያዝያ 18/2018 ዓ.ም

በዋሽንግተን ሂልተን ሆቴል በተካሄደው ዓመታዊ የዋይት ሃውስ የጋዜጠኞች ማህበር የእራት ግብዣ ላይ፣ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በባለስልጣኖቻቸው ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ሙከራ የፈጸመዉ ተጠርጣሪ ነገ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተገለጸ፡፡

ተጠርጣሪዉ የ31 ዓመቱ የካሊፎርኒያ ነዋሪ ኮል ቶማስ አለን በሆቴሉ በፍተሻ ላይ በነበረ የጥበቃ አባል ላይ ሽጉጥ የተኮሰ ሲሆን በጥቃቱ ወቅት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በአስቸኳይ ከስፍራው እንዲወጡ ተደርጓል።

የዩናይትድ ስቴትስ ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቶድ ብላንች ተጠርጣሪው ከሎስ አንጀለስ ወደ ቺካጎ በመጓዝ ከዚያም ወደ ዋሽንግተን እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

ግለሰቡ በሎስ አንጀለስ አቅራቢያ በሚገኝ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበር የተገጸ ሲሆን በፕሬዝዳንቱ እና በካቢኔ አባላቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዱንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ የተተኮሰበት የሚስጥራዊ አገልግሎት አባል ጥይት በማይበሳው ልብስ ምክንያት ሕይወቱ ሊተርፍ እንደቻለና በአሁኑ ወቅት ከሆስፒታል መውጣቱን አረጋግጠዋል።

ተጠርጣሪው በፌዴራል መኮንን ላይ የግድያ ሙከራ በመፈጸም እና የጦር መሳሪያ በመተኮስ ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡

ይህ ክስተት እ.ኤ.አ. ከ2024 ጀምሮ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ሕይወት ላይ የተቃጣ ሶስተኛው የጥቃት ሙከራ ነው። የኔቶ (NATO) መሪ ማርክ ሩተን እና ሌሎች የዓለም መሪዎች ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመበት ሂልተን ሆቴል እ.ኤ.አ. በ1981 በፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገበት ስፍራ መሆኑ ይታወሳል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review