ለስፖርታዊ ውድድሮች ተመራጭ መዳረሻ – አዲስ አበባ

You are currently viewing ለስፖርታዊ ውድድሮች ተመራጭ መዳረሻ – አዲስ አበባ

AMN – ሚያዝያ 20 / 2018 ዓ/ም

አዲስ አበባ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ልዩ ትኩረት እየሳበች ትገኛለች።

ከተማዋ ያላትን የአዘጋጅነት አቅም ፣ የጸጥታ አስተማማኝነትና እያደገ የመጣውን የስፖርት መሠረተ ልማት የሚያሳዩ ኩነቶች በተከታታይ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ድብልቅ የማርሻል አርት ውድድርም ለስፖርት አፍቃሪያን አዲስ አማራጭን ይዞ መጥቷል።

በርካታ ተመልካቾች የታደሙበትን ይህን ልዩ ውድድር የዓድዋ ድል መታሰቢያ በምቹ ሁኔታ አስተናግዷል። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለመሰል ስፖርታዊ ክንውኖች መቹ ስፋራ መሆኑ በፍልሚያ ውድድሩ ታይቷል።

ቅዳሜ ምሽት በታላቅ ድምቀት የተከናወነው የማርሻል አርት ውድድር፣ እንዲህ ያሉ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ዝግጅቶች ለማስተናገድ ከተማዋ ያላትን ምቹነት አረጋግጧል።

ቀደም ብሎ በመዲናዋ የተካሄደው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርም በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል። በርካታ ስመጥር ዓለም አቀፍ አትሌቶች የተሳተፉበት ይህ ውድድር የመዲናዋናን ታላላቅ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ያሳየ ነበር።

በቀጣይም በዚህ ወር ብቻ ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር የተሰኘ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር እና ግራንድ ኢትዮጵያን ረን ውድድሮች በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ይህንን ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኢሊሚኔተር የተሰኘ ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድርን በቀጥታ ያሰራጫል፡፡ ውድድሮቹ አዲስ አበባን በብስክሌት ስፖርት የዓለም ትኩረት እንድትሆን እና በሩጫው ኢትዮጵያ ያላትን የከበረ ዝና የበለጠ የሚያጠናክር መቹ ሆኔታን ይፈጥራሉ።

በከተማዋ ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተሰጠው ትኩረት ፣ አዲስ አበባ ለስፖርታዊ ቱሪዝም እና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እያስቻሏት ይገኛሉ።

በቅርቡ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው በዘመናዊነቱና ለተለያዩ የስፖርት አይነቶች ባለው ምቹነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አዲስ ስፖርት ፓርክ በዚህ ረገድ ይጠቀሳል።

ስልጠናንና መወዳደሪያን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘው የራስ ኃይሉ የስፖርት፣ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ኢትዮጵያ ወደፊት ለምታፈራቸው ስፖርተኞች እንደ ዋና የልህቀት ማዕከል የሚያገለግልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ለመሰል ውድድርም የተመቸ ያደርገዋል።

በከተማዋ እየተስፋፉ ያሉ መሰል ማዕከላት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ ከተማዋ ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎችን ያለምንም እንግልት ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዳላት ማረጋገጫዎች ናቸው።

አዲስ አበባ እያሳየች ያለችው ስፖርታዊ መነቃቃት ከውድድሮች ባለፈ ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው።

ይህ ስኬት፣ መዲናዋ የአፍሪካ የስፖርት ማዕከል ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጋት ሲሆን ፣ በቀጣይ የሚካሄዱት ውድድሮችም ይህንኑ እውነታ ይበልጥ እንደሚያጎሉት ይጠበቃል።

ታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review