አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርገናታል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርገናታል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተሠሩት ሥራዎች መዲናዋን የብልፅግና ተምሳሌትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን እንዳስቻሏት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት እንደገለጹት፣ በከተማዋ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ከማድረግ ባለፈ፣ የሀሳብ ፖለቲካ የሚንፀባረቅባትና የአፍሪካዊያን ኩራት እንድትሆን ማስቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ የብልፅግና ፓርቲ የምስረታ ዓላማንና ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም፣ ፓርቲው ሲመሰረት ለህዝቡ የገባው ቃል ኢትዮጵያን እናበለፅጋታለን የሚል እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም መሰረት አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል ማድረግ መቻሉን ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለዘመናት ወደ ኋላ ያስቀራት ዋነኛው ምክንያት የፖለቲካ ባህል ስብራት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ይህንን አዙሪት ለመስበር ፓርቲው ትልቅ ዋጋ መክፈሉን ገልጸዋል።

ብልፅግና ቂም በቀልን በመተው፣ በውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በማድረግ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ብለዋል።

አዲስ አበባን በተመለከተ በሁለት ጽንፍ የቆሙ የእኔ ብቻ ናት የሚሉ የሀሰት ትርክቶችና የሚዲያ ዘመቻዎች ፈተና ሆነው ቢቆዩም፣ አስተዳደሩ ግን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከተማዋን የሁላችንም ለማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም አዲስ አበባ ከተማ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ 3ኛዋ ትልቋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል እንደሆነች አስታውሰው፣ የኮንፈረንስና የሰላም ከተማ ማድረግ ተችሏል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የፖለቲካ ባህላችንን በሰላማዊ መንገድ መለውጥ ይኖርብናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በአሁኑ ወቅት ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በብሄራዊ ምክክር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለውጡን ለማጣጣል የሚደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ ለአሁኑና ለሚቀጥለው ትውልድ የምትሆን የተሻለች ሀገር ለመገንባት የተጀመረው ጉዞ እንደማይቆም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review