AMN- ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ግንባታ ጉልህ ሚናው ብሔራዊ ኩራትን ከመፍጠር ባለፈ የአፍሪካ አቪየሽን የልህቀት ተምሳሌት መሆኑን የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት ከደንበኞችና አጋሮች ጋር የደንበኞች ተሞክሮ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የአየር መንገዱን አገልግሎት በተመለከተ በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የላቀ ውጤት ያለውና ለረጅም ዓመታት ስኬትን ማስቀጠል ያስቻለ ግዙፍ የመንግሥት የንግድ ኩባንያ ነው።
አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያለው ተቋም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ የሀገር ኩራት የሆነ ሁሉም የኔ የሚለው የጋራ ማንነት መገለጫ ብሔራዊ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ በዘርፉ የመቻልና የልህቀት ማሳያ የሆነ ተቋም መሆኑን አንስተው፣ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ለአገልግሎት ዘርፍ ኤክስፖርት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ ለንግድ መሳለጥና ለሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አየር መንገዱ ግዙፍ የሎጅስቲክስ መሠረተ ልማት አቅም መገንባቱን ገልጸው፥ ለወጪ ንግድ እንዲሁም ለዲፕሎማሲ ትልቅ ሚና ያለው ተቋም ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ ነገን ዛሬ እየገነባ የሚገኝ አኩሪ ኩባንያ መሆኑን መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።