ለ7ኛው ጠቅላላምርጫ የታዛቢዎች መብት ፣ ግዴታና ዝግጅት

You are currently viewing ለ7ኛው ጠቅላላምርጫ የታዛቢዎች መብት ፣ ግዴታና ዝግጅት

AMN – ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውን ለማሳካት የምርጫ ቅስቀሳ፣ ማኒፌስቷቸውን የማስተዋወቅና ሌሎች ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛል፡፡

ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የምርጫው ሂደት ወሳኝ ሲሆን በምርጫ ሂደትም መራጩ ሕዝብ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው የጋራና የተናጠል ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ሆኖ እንዲከናወን በተለይም የሃገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ሚና ጉልህ ሲሆን በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት እና የዕጩ ወኪሎች በታዛቢነት የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡

በተለይም ምርጫን ለመታዘብ የሚመደቡ የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ከቦርዱ ፍቃድ አግኝተው ገለልተኛ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ የሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ሕጋዊ የምስክር ወረቀት ያላቸው ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ሂደቱን የመከታተል፣ መረጃ ጠይቆ የማግኘት፣ የድምፅ አሰጣጥና ቆጠራን የመታዘብ እንዲሁም የታዘቧቸውን ጉድለቶች ለቦርዱ የማቅረብ መብት ተሰጥቷቸዋል።

እንዲሁም ታዛቢዎች የታዛቢነት መታወቂን ይዞ መገኘት፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚሰጧቸውን መመሪያ ማክበር፣ የምርጫው ሂደት በትክክል እንዳይካሄድ ከሚያደናቅፍ ተግባር መቆጠብና ዝርዝር ሪፖርት ለቦርዱ የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎችም በምርጫ ክልልና በጣቢያ ደረጃ ተቀማጭና ተዘዋዋሪ ወኪሎችን መመደብ ይችላሉ።

ታዛቢዎች ከተሰጣቸው የስነ-ምግባር ደንብ ውጭ ሆነው ከተገኙ፣ ምርጫ ቦርድ እንደ ጥፋቱ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ከታዛቢነት እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው።

የታዛቢዎች ሚና በገለልተኝነትና በሕግ አክባሪነት ላይ መመሥረቱ ለምርጫው ስኬትና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሠረት እንደሆነም ይታመናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ለመታዘብ ካመለከቱት የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ውስጥ በሕጉ ላይ የተቀመጠውን መሥፈርት ላሟሉ 55 ድርጅቶች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ድርጅቶቹም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚያሠማሯቸውን 60 ሺህ 277 ወኪሎችን እንዳስመዘገቡ ቦርዱ ገልጹዋል፡፡ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሲያከናውን ቆይቶ በስኬት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 50 ነጥብ 5 ሚሊየን መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያመላክታል፡፡ በአጠቃላይ ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 5 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚሆኑት “በምርጫዬ” የሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት የተመዘገቡ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት ላይ ለሚሠማሩ 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

ቦርዱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ፍቃድ የሰጣቸው የሲቪል ማኅበረስብ ድርጅቶችም ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመራጮች ትምህርት እየሰጡ ይገኛል፡፡

ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መሠረት ያደረገ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮችም እየተካሄዱ ሲሆን፤ የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም የሚካሄድ ይሆናል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review