AMN – ግንቦት 5/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በባህል፣ በኢኮኖሚና በሰላም ማስከበር ዘርፎች በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።
በቅርስ ጥበቃና ልማት ዘርፍ ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጋለች።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በ2011ዓ.ም በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝታቸው ላሊበላን ጎብኝተዋል።
እንዲሁም ባሳለፍነው አመት በታህሳስ ወር በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት፤ ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑን በመግለጽ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

በወቅቱም በከፍተኛ ጥራት የታደሰው የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የአሁኑ ውብ ገጽታ የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከፍተኛ ድጋፍ የታከለበት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፕሬዝዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ስልታዊ የልማት አጋርነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ስምምነቶችንም ተፈርመዋል።
ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ትልቅ ምዕራፍ በሆነው የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ሃገራቱ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር እ.አ.አ 2025 የመጀመሪያውን የሁለትዮሽ መግባቢያ ስምምነት አድርገዋል።

በተጨማሪ በየካቲት 2018 ዓ.ም የ81 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የኢኮኖሚ ድጋፍ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህም ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (HGER 2.0) የ80 ሚሊየን ዩሮ የበጀት ድጋፍ እና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍን ያካተተ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንዲሁም በመጋቢት 2018 ዓ.ም በሰላም ማስከበር ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ስልታዊ አጋርነት ለማሳደግ ያለመ የሁለትዮሽ ስምምነት ፈጽመዋል።
እነዚህ ትብብሮች የሃገራቱ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እና ለቀጣናዊ ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
በትዝታ መንግስቱ