AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
ምዕተ ዓመትን የተሻገረው የኢትዮጵያ-ፈረንሳይ ግንኙነት በታሪክ ከፍ ወዳለ ስትራቴጂካዊ ትብብር አድጓል። የሁለቱ ሐገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል።
በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ መሰማራት የሚፈልጉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። የሐገሪቱ ዋነኛ ሚዲያ ራዲዮ ፍራንስ ኢንትርናሽናሌ በርካታ የፈረንሳይ ኮባንያዎች ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለው የኢትዮጵያ ገበያ መሳባቸውን ዘግቧል።
የፈረንሳይ መንግስት ባወጣው መረጃ መሰረት ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ሶስተኛዋ ትልቋ አውሮፓዊት ሐገር ናት። የፈረንሳይ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት 570 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ነው የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ የሚያመላክተው።
እንደ እርሾ ያሉ ግብዓቶችን የሚያመርተው የፈረንሳይ ለሳፍር(Lesaffre) ግሩፕ እ.ኤ.አ 2021 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወደ ሥራ ገብቶ ይገኛል። “ለሳፍር በኢትዮጵያ ፋብሪካ ለመክፈት የመረጠው ሀገሪቱ በአፍሪካ ሁለተኛዋ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ በመሆኗ እና ነዋሪዎችም የዳቦ አጠቃቀማቸው እያደገ በመምጣቱ መሆኑን የኩባንያው የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማሪን ዱሮት ለራዲዮ ፍራንስ ኢንትርናሽናሌ ተናግረዋል።
በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ አንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ክፍት ስታደርግ ቆይታለች። ኢትዮጵያ ገበያውን ነፃ ለማድረግ ባደረገቻቸው ማሻሻያዎች ምክንያት ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የነበሩ ዋና ዋና ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መወገዳቸውም ይጠቀሳል።
ባለፈው ጥር ወር ታዋቂው የፈረንሳይ ግዙፍ የችርቻሮ ንግድ ድርጅት ካርፎር(Carrefour) የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካል ከሆነው ከክዊንስ ሱፐርማርኬት ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንደሚገባ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። የመጀመሪያዎቹ መደብሮች እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ስማቸውን ቀይረው ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር 15 የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል። ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመልከት ያለመ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ካርፎርን የመሳሰሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ መስፋፋት አዳዲስ የስራ እድሎችን እንደሚፈጥር፣ የክህሎት ሽግግር እንደሚያመጣ እና የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር እንደሚያስተሳስር ነው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚያስረዱት።
በታደሠ ሽፈራው
See less
Boost this post