AMN- ግንቦት 8/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች አዲስ ተስፋን የሰነቀውን፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ደግሞ የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የዛሬ አምስት ዓመት ከነበረው በተሻለ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በማሳደግና ምርታማነትን በመጨመር፣ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬን ማዳን የተቻለበት ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

በፓርኩ ውስጥ ለግብርና ሥራ የሚውሉ ፓምፖች፣ የመኖና የብሎኬት ማቀነባበሪያዎች እንደሚመረቱ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የግብርናው ዘርፍ ከኢንዱስትሪው ጋር ካልተሳሰረ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የተሟላ ሊሆን እንደማይችል አስገንዝበዋል።
በሀገሪቱ ስላለው የሥራ ፍላጎትና በአንዳንድ አካባቢዎች ስለሚታየው የሠራተኛ እጥረት አያይዘውም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እንደ ወንጪ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን እድሳት፣ የጅማ ፕሮጀክቶችና የስኳር ፋብሪካዎች ባሉ በርካታ የልማት ቦታዎች ላይ ሰፊ የሥራ ዕድል ቢኖርም የሠራተኛ እጥረት መኖሩን አንስተዋል።
ወጣቶችም ሥራ የለም ከማለት ይልቅ በእንዲህ ያሉ የልማት ማዕከላት ውስጥ ገብተው ክህሎታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የሚወራውን ብቻ ከመስማት የሚሠራውንም ማየት ተገቢ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ሀገር የሚለወጠው በሥራና በላብ ጠብታ ብቻ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

መንግሥት መሠረተ ልማትን እንደሚያመቻችና ዋናው ሥራ የወጣቱ፣ የአምራቹ እና የባለሀብቱ በመሆኑ ሁላችንም እጅና ጓንት ሆነን ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ዜጎች በሥራ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት ስንችል እውነተኛ የኢኮኖሚ ነፃነት ይረጋገጣል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በሚካኤል ህሩይ