AMN – ግንቦት 12/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባቋቋ መቸው የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ፣ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ያሉ መሰረታዊ ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚሆን የዋጋ ቅናሽ ለሸማቶች እያቀረበ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያከናወናቸው ካሉ ሰፋፊ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማት ጎን ለጎን፣ የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ከተማ አስተዳደሩ ለመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እና ለተለያዩ ዘርፎች ድጎማ የሚውል የ18 ቢሊዮን ብር በጀት በሥራ ላይ መዋሉን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይህም የገበያ ሰንሰለቱን ለማረጋጋት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ 250 የሚደርሱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተደራጅተው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ ከግብርና ምርቶች እስከ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ድረስ በጥራትና በስፋት ምርቶችን እየቀረቡ ይገኛሉ።
በእነዚህ የሕዝብ ገበያዎች ላይ የሚቀርቡ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ ዋጋ ከ15 በመቶ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ እንዳላቸውም ሸማቾች ይናገራሉ፡፡

በነጻው ገበያ ከ2 ሺ ብር በላይ የሚሸጠው የምግብ ዘይት፣ በሸማቾችና በንግድ ሥራዎች ድርጅት አማካኝነት ከ1ሺ 680 ብር ጀምሮ ለሕዝብ እየቀረበ ይገኛል ተብሏል።
ይህ አሠራር ምርትን በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ እንዲደርስ የሚያደርግ በመሆኑ፣ በገበያው መሃል ገብተው ዋጋ የሚጨምሩትን ደላሎች ማስቀረት አስችሏል። ይህም ነጋዴዎች በብቸኝነት ገበያውን እንዳይቆጣጠሩና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ መግታት ተችሏል።
ኤ ኤም ኤን በሰንበት ገበያዎች ላይ የተለያዩ ምርቶችን ሲሸቱ ያነጋገራቸው ሸማቶች በሰጡት አስተያየት ቲማቲም፣ ድንችና ካሮት መሸመታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ይህም ነጋዴዎች ከሚሸጡበት ዋጋ እንደሚረክስ ተናግረዋል፡፡
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹትም ገበያው በቋሚ ዋጋ የሚስተናገድ መሆኑ አማራጭ እንደፈጠረላቸው እና በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ልጆቻቸውን በቅናሽ ዋጋ ለመመገብ እንደረዳቸው ተናግረዋል፡፡

ሸማቾቹ አክለውም፣ ገበያው በአቅራቢያቸው መዘጋጀቱ የትራንስፖርት ወጪን እንዳስቀረባቸው ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም የእሁድና የቅዳሜ ገበያ ቀጣይነት ባለው መልክ በየሳምንቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በወርቅነህ አቢዮ