ከትናንት መደብዘዝ ወደ ነገዋ ሜትሮፖሊታን ከተማነት የምተገሰግስ መዲና

You are currently viewing ከትናንት መደብዘዝ ወደ ነገዋ ሜትሮፖሊታን ከተማነት የምተገሰግስ መዲና

AMN – ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በከፍተኛ ፍጥነትና አስደማሚ ሁኔታ እየተቀየሩ ካሉ ጥቂት ከተሞች መካከል ቀዳሚዋ ሆናለች።

አሮጌውንና ያልዘመነ ገፅታዋን በፍጥነት በማውለቅ ላይ የምትገኘው መዲናዋ ፣ ሰሞኑን በየተራ እየተመረቁና ለአገልግሎት ክፍት እየሆኑ ባሉ ዘመናዊ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ወደ ላቀ የታሪክና የዕድገት ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ ላይ ባደረጓቸው ንግግሮች እንዳረጋገጡት ፣ ፕሮጀክቶቹ መልክ ከመቀየር ባሻገር የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ፣ ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩና አዲስ አበባን የኢኮኖሚና የቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጉ የብልጽግና ማሳያዎች ናቸው።

ከንቲባዋ በንግግራቸው የጠቀሷቸው ዋና ዋና ስኬቶች አዲስ አበባን ወዴት እጅግ እያዘመኗት እንደሆነ በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡

ቀደም ሲል ከምሽቱ 2 እና 3 ሰዓታት ላይ እንቅስቃሴዋ ይደበዝዝ የነበረችው አዲስ አበባ፣ አሁን ላይ ምሽቱን የሚያገለግሉ ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትና የመዝናኛ ኢኮዎች ተፈጥረውላት የሌሊት ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ ሁኔታ እየነቃ ይገኛል፡፡

በከተማዋ የተገነቡ አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ፓርኮችና ሼዶች ከተማዋን ከሸማችነት ወደ አምራችነት እያሸጋገሯት ይገኛሉ።

በተለይም አገር በቀል አምራቾች፣ ወጣቶችና ሴቶች በእነዚህ ዘመናዊ ፓርኮች ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲገኙ አስችሏል።

የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ እና አገር በቀል አምራቾችን በማበረታታት የኢኮኖሚ ጥንካሬን ለመገንባትም ትልቅ መሠረት እየጣሉ ናቸው።

አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች እና አረንጓዴ ስፍራዎችም ሀብታም፣ ደሃ፣ ሕፃን፣ አረጋዊና አካል ጉዳተኛ ሳይለዩ ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠት መቻላቸው ከተመዋን ለነዋሪዎቿ እጅግ ምቹ አድርጓታል።

መዲናዋን የአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት ያደረጉ፣ የወንዞች ዳርቻን ተከትለው የተገነቡ አዳዲስ መዝናኛ ኢኮዎች አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ የቱሪዝም መስህብነት በጉልህ የሚያስተዋውቁ ገጽታዎች ናቸው፡፡

ከንግድና ኢንዱስትሪ ማዕከላቱ መከፈት ጋር ተያይዞ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች፣ ሰፋፊ መንገዶችና የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮችም የከተማዋን መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሱት ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ በከተማዋ እየተገነቡና እየተመረቁ ያሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን ከመጨናነቅ ወደ ተሳለጠ ሥርዓት፣ ከጭስና ከቆሻሻ ወደ አረንጓዴና ጽዱ ሥነ-ምህዳር እና ጥራት ወዳለው ዘመናዊ የከተማ አኗኗር እየለወጧት ናቸው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ደጋግሞ እንደሚያስገነዝበው፣ ይህ የልማት ጉዞ አዲስ አበባን የኢትዮጵያ የብልጽግና ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ አህጉራዊ ኩራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትናፈቅ የነገዋ ሜትሮፖሊታን ከተማ የማድረግ ትልቅ ራዕይ አካል ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረጉ ሰራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የከተማዋን ታሪካዊ ለውጥ ለማስቀጠልና ውበቷንም ለመጠበቅ የነዋሪው ንቁ ተሳትፎና ጥበቃ ወሳኝ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

የመዲናችን አዲስ መልክና የልማት ግስጋሴ የሁላችንም ኩራት ስለመሆኑም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአጽንኦት ያስገነዝባሉ፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review