AMN – ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት እንደተናገሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጽናት፣ የዕድገት እና የጥቁር ሕዝብ የከፍታ ዓርማ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ሀገር ማጽናት የሚቻለው ተቋማትን በማጽናት ነው ብለዋል።

አክለውም በዘመናዊ ታሪካችን የገጠሙን የስብራት ወጀቦችን አልፎ፣ የኢትዮጵያን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ ታሪክ እየጻፈ የተጓዘው አየር መንገዳችን የጽናታችን ግንባር ቀደም ማረጋገጫ ነው።
ለሀገራችንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ በመደገፍ፣ ሀገራችንን በአቪዬሽን መሠረተ ልማት ከፍ በማድረግ፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማገዝና በሌሎች ዘርፎች ባለው ግዙፍ አበርክቶው የዕድገታችን ምሰሶ ሆኗል።

ይህ ተቋም በሁለት እግሩ እንዲቆም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ መሪዎችና ሠራተኞች ነበሩት፤ አሁንም አሉት፣ ወደፊትም ይኖሩታል ብለዋል።
ይህ የተቋሙ አንጡራ ሀብት በመሆኑ የመንግስት ድጋፍና ክትትል ተጥናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።