ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሞዛምቢክን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን

AMN ግንቦት 15/ 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ለመስራት ተቃርቧል። ብሔራዊ ቡድኑ ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ 90 ደቂቃዎች ይቀሩታል።

ከ22 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድኑ ምድብ አንድን ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። ከአዘጋጇ ሞሮኮ ፣ ግብፅ እና ቱኒዚያ ጋር የተደለደለው ብሔራዊ ቡድኑ አራት ነጥብ በመያዝ ነው የምድብ ጨዋታዎቹን ያጠናቀቀው።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ምንም እንኳን ሩብ ፍፃሜ ባይገባም ወደ ዓለም ዋንጫ ለመጓዝ ግን ጥሩ እድል ተመቻችቶለታል።

በዓለም ዋንጫው የአፍሪካ ኮታ 10 ሲሆን ሩብ ፍፃሜ የገቡ ሁሉም ሀገራት ተሳታፊነታቸው ተረጋግጧል። ቀሪ ሁለት ቡድኖችን ለመለየት ምድባቸውን ሦስተኛ ያጠናቀቁ ብሔራዊ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ያከናውናሉ።

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ምድብ ሦስት ላይ ሦስተኛ ሆና ካጠናቀቀችው ሞዛምቢክ ጋር ትጫወታለች። ይህ ወሳኝ ጨዋታ በሞሐመድ ስድስተኛ ኮምፕሌክስ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ይጀምራል።

በጨዋታው አጥቂው ዳዊት ካሳው በቅጣት ምክንያት አይገባም። ሌሎች ተጫዋቾች ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review