የዓለም አቀፍ ትኩረት የሳቡ ስፖርት ማዘወተሪያዎች

AMN ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ የተለመደ አባባል አለ ፤ ውጤት ሲጠፋ ’’አዳጊዎች ላይ መሰራት አለበት’’ የሚል፡፡ በርካቶች ሀረጉን ይደጋግሙታል፡፡ አዳጊ ስፖርተኞች ላይ ለመስራት ምን ያስፈልጋል የሚለው ግን ድምፁ አይጎላም፡፡

በእርግጥ አዳጊዎች ላይ መስራት ለአንድ ሀገር ስፖርት እድገት ትልቅ መሰረት ነው፡፡ለዚህ የስፖርቱ ሳይንስ ያስቀመጣቸውን መንገዶች ተከትሎ መስራት አዋጭ ይሆናል፡፡ ሌሎች በርካታ ግብዓቶች እንዳሉ ሆነው ለውጤታማነቱ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ዋነኛ መሠረት ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ስፖርት ምን ማምጣት እንደሚችል መንግሥት በሚገባ ተረድቷል፡፡ አዲስ አበባ ለዚህ ቀዳሚውን ስፍራ ትወሰወዳለች፡፡ ከዚህ ቀደም መኪና መጣ አልመጣ በሚል ስጋት ይጫወቱ የነበሩ አዳጊዎች አሁን እፎይታ አግኝተዋል፡፡ የኮሪደር ልማት ተግባራዊ ሲሆን በየቦታው የስፖርት ማዝወተሪያ ስፍራዎች አብረው ተገንብተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የልማቱ አንድ አካል ተደርጎ ያልተቆጠረው ስፖርት በዚህ ልክ ቦታ ማግኘቱ ለበርካቶች አስደሳች ነበር፡፡ ልጆች ይቦርቁባቸው የነበሩ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ለህንፃ ግንባታ ሲውል ያየ የከተማዋ ነዋሪ ስራውን አድንቋል፡፡ የስፖርት ፍላጎት እና ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች አሁን በማዘወተሪያ እጥረት ወደ ኋላ አይቀሩም፡፡

ትሩፋቱ ለልጆች ብቻ አይደለም የተረፈው ፤ ራሳቸውን አብቅተው እንጀራቸውን የመሰረቱ ስፖርተኞችም ጭምር እንጂ፡፡ ጤናዬን ልጠብቅ ያለም ወደ ማዘወተሪያዎቹ ጎራ ብሎ ያሻውን ማድረግ ይችላል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በስፋት መገንባታቸው ጥቅሙ በግልፅ እየታየ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እንዳወጣው መረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ለአዳጊ ወጣቶች ስልጠና የሚሰጡ 723 አዳዲስ ጣቢያዎች ተከፍተዋል፡፡ ከ89 ሺህ በላይ አዳጊዎች በጣቢያዎቹ ስልጠና እየወሰዱም ይገኛል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 063 ስፖርተኞች ከፍ ያለ ደረጃ ደርሰው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፣ ለክለቦች እና ለአካዳሚዎች መመረጥ ችለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም የተሰጠው ትኩረት በግልፅ ይታያል፡፡ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዳጋራው መረጃ ከመንግስት ለውጥ በፊት 27ሺህ 539 የነበረው የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች ብዛት ወደ 45ሺህ 175 ማደግ ችሏል፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ 17ሺህ 636 ትንንሽ ሜዳዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ታላላቅ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች እንድታዘጋጅ እድል ሰጥቷታል፡፡ ደረጃውን የጠበቀው የአዲስ አበባ ስታዲየም መም ኢትዮጵያ ታሪካዊ ውድድር እንድታዘጋጅ በር ከፍቷል፡፡ የነሐስ ደረጃ ያገኘው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ በድምቀት ተከናውኗል፡፡ በዝግጅቱ እንዲሁም በስፖርት አፍቃሪው ደማቅ አቀባበል የተማረኩት የዓለም አትሌቲክስ ሃላፊዎች ውድድሩ በወርቅ ደረጃ አድጎ በቀጣይ ዓመት እንዲካሄድ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡

ሲቲ ማውንቴን ኢሊሚኔተር ፕሮ ሊግ እንዲሁም የአፍሪካ የዞን አምስት የእጅ ኳስ ውድድር ሌሎች ትኩረት ያገኙ እና የዓለምን ዓይን ወደ አዲስ አበባ ያዞሩ ስፖርታዊ ሁነቶች ናቸው፡፡

ስፖርት ለሀገር ገፅታ ግንባታ ያለው ሚና በሚገባ የተገነዘበው መንግስት ውድድሮቹን በብቃት ማዘጋጀቱ ሌሎች እንዲሳቡ ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን እየገነባች ካለው አቅም መነሻ ታላለቅ ውድድሮችንም ለማዘጋጀት ጥያቄ እያቀረበች ትገኛለች፡፡

በእግርኳሱ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ፤ በአትሌቲክሱም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማሰናዳት ፍላጎት ከማሳየት ተሸግሮ ወደ ተግባር ገብታለች፡፡ ከተሳካም ኢትዮጵያ በስፖርቱም የስበት ማዕከልነቷን የበለጠ ታሰፋለች፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review