AMN ግንቦት 20/2018
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያካሄዱት የምርጫ ክርክር መራጩ ህዝብ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያደርግ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ገለጹ።
ቦርድ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ማጠናቀቂያ እና የጥሞና ጊዜ ማብሰሪያ መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በምርጫው ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያደርጉ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ እንዲካሄድ ተደርጓል።
ቦርዱ በክርክር ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጠና መስጠቱን አመልክተው፤ ክርክሩ በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲመራ መደረጉን ጠቁመዋል።
በምርጫ ክርክር ሂደቱ የሚነሱ ሃሳቦች እውነታን ለማረጋገጥ ሀቅ የሚያጠራ (ፋክት ቼክ) የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ መደረጉንም ተናግረዋል።
በምርጫ ክርክሩ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሀሳቦቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ የምርጫ ክርክር መድረኩ መራጩ ህዝብ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ክርክሩ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እና ባለሙያዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፤ የምርጫ ክርክሩ ዲሞክራሲያዊ በሆነ እና የገለልተኝነት መርህን ጠብቆ መካሄዱን አስረድተዋል።

ክርክሩ በ19 ዙር መካሄዱን ጠቁመው፤ በክርክሩ 33 ፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን አብራርተዋል።
ክርክሩም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዲጂታል አማራጮች ለመራጩ ህዝብ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።
የክርክር መድረኩ ለቀጣይም ግብዓት የሚሆን እውቀት እና ልምድ የተገኘበት መሆኑን ነው ምክትል ሰብሳቢው ገልጸዋል።