የዘመናት እንቆቅልሽ፤ ለዓመታት የማይበላሸው የተፈጥሮ “ወርቅ” ማር

AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ማር በንቦች አማካኝነት ከአበቦች የአበባ ማር ተዘጋጅቶ የሚቀመጥ፣ በካርቦሃይድሬት የበለፀገ ወፍራም እና ጣፋጭ ፈሳሽ ነው።

ጊዜ ሁሉንም ነገር ይለውጣል፤ ምግቦችን ያበላሻል፣ ብረትን ያዝጋል፣ ድንጋይን ይሸረሽራል። ነገር ግን የጊዜ ህግ የማይሰራበት አንድ ተፈጥሯዊ ተአምር አለ፤ እሱም ማር ነው።

ማር ምግብ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሺህ ዓመታት ለሕክምና እና ለተለያዩ ባህላዊ አገልግሎቶች ሲውል የቆየ የተፈጥሮ በረከት ነው።

ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት በጥንታዊ ግብፃውያን ፈርኦኖች መቃብር ውስጥ የተቀመጠ ማር፣ ዛሬም ድረስ ሳይበላሽ ለምግብነት ዝግጁ ሆኖ መገኘቱ የሳይንስ ዓለምን ያስገረመ ትልቅ እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቷል።

ይህ የተፈጥሯዊ ጣፋጭ ለዓመታት ሊኖር የቻለበትን ምስጢር የሳይንስ ሊቃውንት በሚከተሉት ሶስት አስደናቂ ምክንያቶች ይተነትኑታል።

የመጀመሪያው ማር በተፈጥሮው ዝቅተኛ የውሃ መጠን ያለው ምግብ ሲሆን ማንኛውም ባክቴሪያ ወደ ማር ውስጥ ቢገባ፣ ማሩ በውስጡ ያለውን እርጥበት በ”ኦስሞሲስ” አማካኝነት ስለሚመጥበት ባክቴሪያው ሳይራባ ወዲያውኑ እንዲሞት ያደርገዋል።

በሌላ አባባል ማር ባክቴሪያዎች የሚታነቁበት ደረቅ እስር ቤት እንደሆነ ነው ሊቃውንቶች የሚያስረዱት፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የማር “የፒ ኤች” መጠን አሲዳማነት ባህሪ አለው። ይህ ከፍተኛ አሲዳማነት ደግሞ ማንኛውም ረቂቅ ተህዋሲያን በውስጡ እንዳይኖሩ እንደ መከላከያ ግንብ ሆኖ ያገለግላል።

ሌላው ምክንያት ንቦች የአበባ ማር በሚሰበስቡበት ወቅት ከሰውነታቸው ውስጥ “ግሉኮስ ኦክሲዴዝ” የተባለ ኢንዛይም ይጨምሩበታል።

ይህ ኢንዛይም በኬሚካላዊ ሂደት “ሃይድሮጅን ፐሮክሳይድ” የተባለ ተፈጥሯዊ ፀረ-ተባይ ያመነጫል። ይህም ማሩ ለማንኛውም ተላላፊ ተህዋሲያን የማይበገር እንዲሆን እንደሚያደርገው የሳይንስ ሊቃውንቱ አመላክተዋል፡፡

ብዙዎች ማር ሲረጋ ወይም ወደ ስኳርነት ሲቀየር የተበላሸ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሳይንሱ እንደሚለው ይህ “ክሪስታላይዜሽን” የተፈጥሮ ሂደት እንጂ የመበላሸት ምልክት አይደለም። ማሰሮውን ለጥቂት ደቂቃ ለብ ባለ ውሃ ውስጥ በማስቀመጥ ማሩን ወደ ቀድሞ ይዘቱ መመለስ ይቻላል።

በአጠቃላይ ማር ምግብ ብቻ አይደለም፤ የተፈጥሮ ድንቅ ምህንድስና ውጤት እንጂ! ዛሬ በገበታዎ ላይ ያለው ማር፣ በትክክል ካስቀመጡት ለልጅ ልጅዎ ሊተርፍ የሚችል ብቸኛው የምድር ምግብ ነው።

እናንተስ ማር ሲረጋባችሁ ተበላሸ ብላችሁ ደፍታችሁ ታውቃላችሁ? ወይስ ይህን የተፈጥሮ ምስጢር ቀድማችሁ ታውቁ ነበር? በኮሜንት ያጋሩን!

በወርቅነህ አቢዮ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review