የእንጦጦ-ቀጨኔ ፕሮጀክት የሀገር በቀል እውቀትና የፈጣን እድገት ማሳያ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለውን የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ስራ አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት ፣ ፕሮጀክቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንና የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና አለው።

ከእንጦጦ ቁስቋም እስከ ቀጨኔ ያለው የ 9.6 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት የእግር ጉዞን ጨምሮ እጅግ ማራኪና ለማመን የሚከብዱ ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው የተጀመረው የከተማ እርሻ ሙከራ አስገራሚ ውጤት ማሳየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የእንጆሪ ፣ የብርቱካን ፣ የሎሚ፣ የደጋ ቡና እና ልዩ መአዛ ያለው የእንጦጦ ማር ምርት ልማት ከሐገር ውስጥ ባሻገር ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ትልቅ አቅም እንዳለው አመልክተዋል።

የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ ከፍተኛ ውሃ የሚመጠውን ባህር ዛፍ በሀገር በቀል ዛፎች የመተካት ስራ እየተሰራ ይገኛል። ይህ ለውጥ ተራራው ውሃ የመያዝ እና ለታችኛው ተፋሰስ እርጥበት የመልቀቅ አቅሙን ከወዲሁ እንዳሳደገው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተራራማው አካባቢ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የተሰሩትን አስደናቂ እርከኖች በተለይ አድንቀዋል።

በፍጹም ከማሽን ውጪ ሰው ይገነባዋል ተብሎ በማይታመን ደረጃ እርከኖቹ የተሰሩት ከውጭ በመጡ ሳይንቲስቶች ሳይሆን በኮንሶ እጅ የሀገር ውስጥ ሙያተኞች ነው።

በገጠር ያለው የሀገራችን ነዋሪ ለከተማው የሚያበረክተው እውቀት እንዳለ ያየሁበት ነው ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የገጠሩን እውቀት ለከተማ፣ የከተማውን ለገጠር በማምጣት ሀገራችንን ማሳመር እንችላለን ብለዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢው በፕላስቲክ የተሰሩ፣ ለክረምት ጎርፍና ለአደጋ የተጋለጡ፣ መጥፎ ጠረን የነበራቸውና የመኪና መንገድ የሌላቸው የታጨቁ ቤቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲሱ ፕሮጀክት ግን ይህንን ታሪክ ሙሉ በሙሉ በመቀየር የመንቀሳቀሻ ተደራሽነት የፈጠረና የሰዎችን የኑሮ ዘይቤ ያሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእንጦጦ እስከ ቦሌ ያለው የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት በአብዛኛው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የቀሩት ክፍሎች ደግሞ በሚቀጥሉት 2 እና 3 ወራት ውስጥ ተጠናቀው እስከ ፒኮክ ያለው መስመር ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ እንደሚውል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብስረዋል።

እድገት፣ ልማትና ለውጥ ለመጎናጸፍ ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው መሆኑንና እሱም ተግቶ መስራት፣ ሳይሰንፉ ተግቶ መሮጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review