AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም

በትዳር ሕይወት ውስጥ ትልቅ ፈተና ከሚሆኑና ማኅበራዊ ቀውስ ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ መካንነት ነው።
በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጥንዶች ይህንን ፈታኝ ችግር በዝምታና በከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጭንቀት ውስጥ ሆነው ይጋፈጡታል።
በሕክምናው ትርጓሜ መሠረት፣ አንድ ባልና ሚስት ምንም ዓይነት የወሊድ መከላከያ ሳይጠቀሙ፣ መደበኛ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እያደረጉ ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ እርግዝና መፍጠር ካልቻሉ ሁኔታው መካንነት ተብሎ ይፈረጃል።
ይህ ሁኔታ በአብዛኛው በአንደኛው ወገን፣ በተለይም በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ተደርጎ የመውሰድ የተሳሳተ ማኅበራዊ ግንዛቤ ቢኖርም፣ የሕክምና ሳይንስ ግን እውነታው ሌላ መሆኑን ያረጋግጣል።

በጥናት የተደገፉ የሕክምና መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የመካንነት ችግር 33 በመቶ በሴቶች የጤና እክል፣ 33 በመቶ በወንዶች የጤና እክል፣ እንዲሁም ቀሪው 34 በመቶ በሁለቱም ጥምር ችግሮች ወይም በምርመራ በግልጽ በማይታወቁ ልዩ ልዩ መንስኤዎች የሚከሰት ነው።
በሴቶች ላይ ለሚከሰተው መካንነት ዋነኞቹ ምክንያቶች በሆርሞን መዛባት ወይም ፒ.ሲ.ኦ.ኤስ (PCOS) በተባለ የጤና እክል ሳቢያ መደበኛ እንቁላል በአግባቡ ሳይለቀቅ ሲቀር ነው።
በተጨማሪም በተለያዩ የውስጥ አካላት ኢንፌክሽኖች ምክንያት የማኅፀን ቱቦ መዘጋት ወይም መደፈን ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከዚህ ባለፈም፣ የማኅፀን ዕጢዎች መኖር ፅንስ በማኅፀን ግድግዳ ላይ እንዳይቀመጥ በማድረግ ረገድ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።
በወንዶች በኩል ደግሞ የዘር ፍሬ (የስፐርም) ጥራትና ብዛት ማነስ ለችግሩ ግንባር ቀደም መንስኤ ነው። ይህም የስፐርም ቁጥር ማነስን፣ የፍጥነት ደካማ መሆንን ወይም መዋቅራዊ ቅርፅ መበላሸትን ያጠቃልላል።
ሌላውና ዋነኛው ምክንያት በወንድ የዘር ፍሬ ከረጢት ውስጥ ያሉ የደም ሥሮች ማበጥ ወይም ቫሪኮሲል ሲሆን፣ ይህም የዘር ፍሬውን ሙቀት በመጨመር የስፐርም ምርትን በእጅጉ ያሰናክላል።

ከጤና እክሎች ባለፈ፣ ከዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ለችግሩ መከሰት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
በዚህም መሠረት ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት ወይም በድንገት ክብደት መቀነስ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮልና ጫት አዘውትሮ መጠቀም፣ እንዲሁም የወንድ የዘር ፍሬን ለከፍተኛ ሙቀት ማጋለጥ ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
የሕክምና ሳይንስ ፈጣን ዕድገት ልጅ መውለድ ለሚናፍቁ ጥንዶች በርካታ አዳዲስ ተስፋዎችንና መፍትሔዎችን ይዞ መጥቷል።
ከእነዚህም መካከል የሆርሞን መዛባትን በማስተካከል ሴቶች መደበኛና ጤናማ እንቁላል እንዲያመርቱ መርዳት አንዱ ሲሆን፣ የተዘጉ የማኅፀን ቱቦዎችን ለመክፈት ወይም የወንዶችን የቫሪኮሲል ችግር ለማስተካከል የሚደረጉ የቀዶ ሕክምናዎችም ሌላው አማራጭ ናቸው።
የወንዱን ስፐርም በቤተ-ሙከራ በማጥራት፣ በቀጥታ ሴቷ እንቁላል በምትለቅበት ቀን ማኅፀን ውስጥ የማስገባት የአይ.ዩ.አይ (IUI) የሕክምና ዘዴ እንዲሁም እንቁላልና ስፐርምን ከጥንዶቹ በመውሰድ በቤተ-ሙከራ ውስጥ እንዲዋሃዱ በማድረግ የዳበረውን ፅንስ ወደ ማኅፀን የመመለሱ እጅግ ስኬታማው የአይ.ቪ.ኤፍ (IVF) ቴክኖሎጂ ውጤት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እየሰጡ ይገኛሉ።
መካንነት ሊታከም የሚችል ፈታኝ የጤና እክል እንጂ እርግማን ወይም የአንዱ ወገን ብቻ ጥፋት ባለመሆኑ፣ በትዳር ውስጥ ይህ ችግር ሲያጋጥም መወቃቀስን አስወግዶ፣ በጋራ ወደ ሕክምና ባለሙያ መሄድና እርስ በርስ በሥነ-ልቦና መደጋገፍ ቀዳሚውና ዋነኛው የመፍትሔ እርምጃ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በበረከት ጌታቸው