ምክር ቤቱ የብድር ስምምነቶችን አፀደቀ

You are currently viewing ምክር ቤቱ የብድር ስምምነቶችን አፀደቀ

AMN ግንቦት 27/ 2018 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው 23ኛ ጉባኤው በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ለአርብቶ አደሩ የምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለስድስተኛ ምዕራፍ የልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክት የተደረገ የብድር ስምምነትም ምክር ቤቱ አፅድቋል።

የብድር ስምምነቶቹን በማስመልከት በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ለአርብቶ አደር ምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተገኘው ብድር መንግስት የአርብቶ አደሩን የህበረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ የበለጠ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

‎በተለይም በ30 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የአርብቶ አደሩን የምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ዋና ተጠሪው አብራርተዋል፡፡

‎ሚኒስትሩ አክለውም ይህንን የልማት ተግባር ይበልጥ ለማጠናከር እና በክፍል አንድ ያልተካተቱትን ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን በማካተት የአርብቶ አደሩን የአደጋ ተጋላጭነትን መቋቋም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በአፍሪካ ልማት ባንክ 71 ሚሊዮን 940 ሺ የአሜሪከ ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

‎በብድር የተገኘው ገንዘብ የውሃ መሰረተ ልማቶችን፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን፣ ዘላቂ የመሬት አያያዝን፣ አግሪ ቢዝነስ ልማትን፣ ታዳሽ የኃይል አማራጭችን እና የአየር ትንበያ ጣቢዎችን ለማስፋፋት እንደሚውል ገልፀው፤ ብድሩ ከወለድ ነጻና የአስር ዓመት ችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

‎የብድር ሥምምነቱ ከአገራችን የብድር ስትራቴጅ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣምና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያይዙ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስና የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ፣ አዋጅ ቁጥር 1423/2018 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

‎በተያያዘም የመንግስት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያና በዓለም ዓቀፍ ልማት ማህበር መካከል ስድስተኛውን ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት በማስመልከት ገለጻ ሰጥተዋል።

‎መንግስት በምግብ ዕጥረት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተስብ ክፍሎችን ከዕርዳታ ተጠቃሚነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ባለፉት ጊዜያት የልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክትን ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል።

ስድስተኛው ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት በ12 ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ባሉ 494 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ከምክር ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review