ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የድርሻውን ጠጠር ለመጣል በምርጫ መሳተፉ የዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ዋነኛ አካል መሆኑ ተገለጸ

AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ህዝብ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በውጭ ኃይሎች የሚነዛውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን በመተውና ትልቁን ሀገራዊ ስዕል በማየት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳየው ተሳትፎ ታሪካዊ ነው ሲሉ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ኪያ ፀጋዬ ተናገሩ።

ከ54 ሚሊየን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ምርጫው ሀገረ መንግሥትን ለማጽናት እና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ዳር የሚያደርስ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ወሳኝ መሆኑ ጠቁመዋል።

የሕግ አማካሪና ጠበቃ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ኪያ ፀጋዬ ከኤ ኤም ኤን ሰንኮፍ የቴሌቪዥን መሰናዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት አንድን ሀገር ሀገር የሚያሰኙት ግዛት፣ ህዝብ፣ መንግስት እና ዓለም አቀፍ እውቅና ናቸው፡፡

በዚህም ህዝብን የሚወክል መንግስት ወቅቱን በጠበቀ ምርጫ ማቋቋም ካልተቻለ ሀገረ መንግስትን መገንባት አይቻልም፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም፣ በፍትሃዊ መንገድ ወደብ የማግኘት ጥያቄ እንዲሁም ከታሪካዊ ዳራዋ አኳያ ከቅርብም ከሩቅም በበርካታ ጫናዎች የተከበበች መሆኗ የገለጹ ሲሆን ህዝቡ ይህንን ተገንዝቦ በውጭ ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል ለሀገሩ ድምፁን መስጠቱ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ አብራርተዋል።

ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ሽግግር ወሳኝ ናቸው ያሉት የህግ ምሁሩ በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የአዲሱ የኤርፖርት ግንባታ፣ የኤክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና ሌሎች መሰል ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጠንካራ የቁጥጥር እና የማስፈጸም አቅም ያለው መንግሥት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለዚህ ሀገራዊ ግብ መሳካት እና መንግሥትን ለማቋቋም ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ያደረገ አስተዋጽኦ የላቀ እና ታሪካዊ ነው ብለዋል።

ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የድርሻውን ጠጠር ለመጣል በምርጫ መሳተፉ የዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ዋነኛ አካል መሆኑንና፤ በሂደቱ ሳይሳተፉ ቅሬታ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review