AMN- ሰኔ 4/2018 ዓ.ም
የ2026 የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ሀገራት በጣምራ የሚያዘጋጁት ፣ 48 ሀገራት በ12 ምድብ ተከፍለዉ የሚፋለሙበት መድረክ ነው
ይህ ታሪካዊ ዓለም ዋንጫ ዛሬ በይፋ ሲጀምር ከአስተናጋጆቹ አንዷ ሜክሲኮ ደቡብ አፍሪካን ምሽት 4 ስዓት ላይ በኢስታዲዮ አዝቴካ የምታስተናግድ ይሆናል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ የደመቀ የተሳትፎ ታሪክ ቢኖራቸዉ ዋንጫዉን የመሳም እድል ግን አላገኙም፡፡
በአለም ዋንጫ ታሪክም በመክፈቻ ጨዋታ ከ2010 በኋላ የተገናኙበት መድረክ የሚሆንበት ምሽት ሲሆን በወቅቱ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት መላያየታቸው ይታወሳል፡፡

ሜክሲኮ በዓለም ዋንጫ ባለፉት ሰባት የመክፈቻ ግጥሚያዎቿ አልተሸነፈችም። በአንጻሩ ደቡብ አፍሪካ በዘጠኝ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች አንድም ጎል አለማስቆጠሯ ምን ያህል ደካማ ታሪክ እንዳላት የሚያሳይ ነው።
በጃቪየር አጉየር የምትመራው ሜክሲኮ የዛሬው ጨዋታ የማሸነፍ ቅድመ ግምትን አግኝታለች፡፡
ሜክሲኮ በዓለም ዋንጫ ለ18ኛ ጊዜ የምትካፈል ሲሆን በዞኑ የኮንካካፍ ሀገራት በርካታ ጊዜ በመሳተፍ የሚቀድማት የለም።
ብሔራዊ ቡድኑ በታሪኩ እ.ኤ.አ በ1970 እና በ1986 የአለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሱበት ትልቁ ዉጤታቸው ነው፡፡
ከውድድሩ በፊት አብዛኛው ትኩረት አጥቂዉ ራውል ሂሜኔዝ የሜክሲኮን መስመር እንዴት እንደሚመራ ያተኮረ ሲሆን አርብ ዕለት በተደረገው የመጨረሻ የቅድመ-ውድድር ጨዋታ ሰርቢያን 5-1 ሲያሸንፍ አጥቂው ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በሁጎ ብሩስ የምትመራዉ ደቡብ አፍሪካም ለሜክሲኮ ቀላል ተጋጣሚ ትሆናለች ተብሎ ባይገመትም በምሽቱ ጨዋታ ልምድ ያላቸዉ እና ወጣት ተጨዋቾቿን ታጣምራለች፡፡
ሌላኛው ጨዋታ በዚሁ ምድብ አንድ የሚገኙት ደቡብ ኮሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ነው። ጨዋታው ሌሊት 11:00 ይጀምራል።
በአለማየሁ ሙሳ