AMN – ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያዊያን ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀር እና ሀገሪቱን የአፍሪካ ቀዳሚ የህክምና ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርግ ግዙፍ የህክምና ተቋም ትላንት ተመርቋል።
በ5.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውንና በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ይህንን ሆስፒታል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በታላቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቆ ተከፍቷል።
የዚህ ሆስፒታል መገንባት ዋናውና ልዩ ጠቀሜታው፤ ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ ባለመኖራቸው ምክንያት ዜጎች ከፍተኛ ወጪና የውጭ ምንዛሬ አውጥተው ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚገደዱባቸውን እንደ ካንሰር እና ውስብስብ የልብ ህክምና ያሉ ከባድ የጤና እክሎችን እዚሁ ማከም ማስቻሉ ነው።

ይህ ተቋም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀየር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ራሷን ለመቻልና ለሀገራዊ ልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ሆኗል።
ሆስፒታሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ የዲጂታል የቅድመ እና ድህረ ካንሰር ምርመራ ማሽንን ጨምሮ እጅግ የረቀቁ የቴክኖሎጂ አቅሞችን አካቷል፡፡
ባለ 3-ቴስላ ኤም.አር.አይ (3-Tesla MRI) እና ባለ 640-ስላይስ ሲቲ ስካን (640-slice CT scan) ማሽኖች፣ በድምጽ ትዕዛዝ ብቻ የሚሰራ የካቴተራይዜሽን ላብራቶሪ (Cath Lab) እንዲሁም የ3ዲ (3D) ማሞግራፊ እና የሮቦቲክስ ላብራቶሪ (TLA) መሳሪያዎች የተደራጀም ነው።
የማዕከሉን ምረቃ አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በሕክምና ትምህርትና በጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ዘርፍ በአፍሪካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ከ400 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የስፔሻላይዝድ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙና ይህም የሀገሪቱን የሕክምና ተቋማት በአህጉሪቱ ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ከዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች መሟላት ባለፈ የአገልግሎት ጥራትና የዜጎች እርካታ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዜጎች ወደ ሆስፒታሉ በሚመጡበት ወቅት በክብር፣ በታላቅ ትህትና እና በፈገግታ ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በትምህርት ቤት ምገባና በአስተማሪዎች ብቃት ዙሪያ የተመዘገቡት ስኬቶች በጤናው ዘርፍም እንዲደገሙ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በበረከት ጌታቸው