“አለንጌ” – ለዘመናዊዉ ዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆነ የኦሮሞ ህዝብ የሥልጣን ርክክብ ባህላዊ ሥርዓት

You are currently viewing “አለንጌ” – ለዘመናዊዉ ዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆነ የኦሮሞ ህዝብ የሥልጣን ርክክብ ባህላዊ ሥርዓት

AMN – ሰኔ 05/2018 ዓ.ም

በዩኔስኮ ዕውቅና ያገኘው የገዳ ሥርዓት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ለሕግ ያለው ክብር እና የጋራ ውሳኔ አሰጣጥ ለዓለም የተረጋገጠ እውነት ነው።

አለንጌው በዚህ ታሪካዊ ቀን ሲተላለፍ፣ የሕዝብ ሉዓላዊነትና የሰላም ጉዞ በአዲስ ምዕራፍ ይቀጥላል።

በቱለማ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ “አለንጌ” ማለት እንዲሁ ቁስ አይደለም አለንጌ በኦሮሞ ሕዝብ አኗኗር ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው የተፈጥሮ ምልክት ነው።

ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በግለሰብና በማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ጥቅም ላይ ይውላል። ይህም የካሳ ሥርዓት፣ የገዳ ሥርዓት፣ ጋብቻ እና የዕርቅ ሥርዓትም በአለንጌ ይፈጸማል።

በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚከናወነው የአለንጌ ርክክብ፣ የሥልጣን ሽግግርን ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝብን ቃል ኪዳን፣ የፍትሕን ልዕልና እና የትውልድ ቅብብሎሽን የሚያበስር ልዩ ምልክት ነው።

በየስምንት ዓመቱ በሚደረገው የአመራር ሽግግር ወቅት ከአባ ገዳ ወደ አባ ገዳ የሚተላለፈው የሚጨበጠው አለንጌ ብቻ ሳይሆን፣ በዋናነት ሕዝብን በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነት የያዘ የአደራ ስልጣን ጭምር ነው፡፡

አባ ገዳዎች ቢቀያየሩም፣ በገዳ ሥርዓት የሚተዳደሩት እሴቶች ግን ሳይለወጡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሻግራሉ። በተጨማሪም ይህ ሥርዓት ማኅበረሰቡን በተጠያቂነት፣ በመግባባት እና በሰላም ሲመራ የቆየው የገዳ ሥርዓት ሕያውነት መገለጫ እሴቶች ይዞ የሚጓዝ ነው።

በአሁኑ ወቅት የቱለማ ኦሮሞ የገዳ አመራር ሽግግር ሂደት ላይ ይገኛል። የሜልባ ገዳ ወደ ሙዳና ገዳ የሚያደርገው 71ኛው የቱለማ ገዳ የአለንጌ ርክክብ ታሪካዊ ሥርዓት ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በደካ ኮራ (የባህላዊ ሥነ-ሥርዓት ማከናወኛ ስፍራ) እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

በዩኔስኮ ዕውቅና ባገኘው የገዳ ሥርዓት አማካኝነት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ለሕግ ያለው ክብር እና የዴሞክራሲያዊ አሠራር ለዓለም ማሳያ ሆኖ ይቀጥላል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review