AMN- ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
የቦሌ ቡልቡላ ፓርክ ከመዝናኛ ባሻገር የነዋሪዎችን ማህበራዊ ትስስር እያጠናከረ ይገኛል፡፡
ወ/ሮ ራህማ መሐመድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በእረፍት ቀናቸው ወደ ተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች መሄድን ያዘወትራሉ፡፡
ከዚህ በፊት አንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርክን እንደተመለከቱ በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ቦሌ ቡልቡላ መዝናኛ ፓርክም በመምጣት የማይረሳ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ያነሳሉ፡፡
በተለይም ቅዳሜ እና እሁድ ልጆቻችንን እንዲሁም ከጅቡቲ፣ ከየመን እና ከሌሎች ሃገራት የሚመጡ ዘመዶቻቸውን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎችን ጭምር ይዘን በመምጣት በፓርኩ ውስጥ ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን ይላሉ፡፡

ከተለያዩ ሃገራት መጥተው የተለያዩ መዝናኛዎችን የሚጎበኙ ዜጎችም ደስተኞች መሆናቸውን ይነግሩናል የሚሉት ወ/ሮ ራህማ በሌሎች አካባቢዎችም አዳዲስ መዝናኛ ስፍራዎች እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
አዲስ አበባን እንደዚህ ውብ ሆና በማየቴ ደስተኛ ነኝ፤ ይሄንን የሰሩትን እናመሰግናለን፣ ሰላም እና ፍቅር ካለ ደግሞ ከዚህ የበለጠ መስራት እንደሚቻል አይተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም በትብብር ከሰራ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ማደግና መልማት እንደምትችልም ተመልክተናል ሲሉ ወ/ሮ ራህማ ይናገራሉ፡፡

ሌላኛው በቦሌ ቡልቡላ ፓርክ ከልጆቻቸው ጋር ሲዝናኑ ያገኘናቸው አቶ አሰፋ ክዚ ልጆች የእረፍት ቀናቸውን ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ ወደ መዝናኛ ፓርኩ መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በፓርኩ ውስጥ የህጻናት መጫወቻ፣ የወጣቶችና የአዋቂዎች መዝናኛ እንዲሁም የእግር ኳስ መጫዎቻ መኖሩን በማንሳት በመዝናኛ ስፍራዎቹ ከመዝናናቱ ባለፈ ማህበራዊ ትስስርንም እያጠናከርን ነው ይላሉ፡፡
በመሆኑም ወላጆች በእረፍት ቀናቸው ለልጆቻቸው ጊዜ ሰጥተው በመዝናኛ ስፍራዎች ቢያሳልፉ ለልጆች አእምሮ እድገት ወሳኝ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ከመኖሪያ አካባቢችን በቅርብ ርቀት ይሄ መኖሩም ከትራንስፖርት ወጭ አድኖናል የሚሉት አቶ አሰፋ፤ መዝናኛ ፓርኩ ለልጆችና ለአዋቂዎች ጤና ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ትውልዱ ስለ ሃገሩ በቂ እውቀት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አእምሮን የሚያድሱና የሚጎበኙ በርካታ ስፍራዎች እንዳሉም ተገልጋዮች ያነሳሉ፡፡
በየሻምበል ምህረት