AMN- ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመጡ እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገኝተው ታሪካዊ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በጉብኝታቸው ስለ ዓድዋ ገድል የሰሙት ታሪክ እንዳስደነቃቸው ገልጸው፣ መታሰቢያው ይህንን ታላቅ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በዚህ መልኩ መደራጀቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከብሪቲሽ ኤንባሲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ዲፕሎማቶችን በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊና ሰው ሠራሽ መዳረሻዎችን ያስጎበኘ ሲሆን፣ ጉብኝቱም አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ የቱሪስት እና የኮንፈረንስ መዳረሻ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ከጎበኟቸው የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ አንዱ ሲሆን፣ መታሰቢያው አያቶች እና ቅድመ-አያቶች የከፈሉትን መስዋዕትነትና የነፃነት ተጋድሎ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እና ከታሪኩ ባለቤት በላይ ለነፃነት ለሚታገል ማንኛውም ሕዝብ ሥፍራው ትልቅ የብርታት ምንጭ እንደሆነ መናገራቸውን ከአድዋ ድል መታሰቢያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ይህ ጉብኝት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄደው 4ኛው የዲፕሎማቲክ ዋንጫ ስፖርታዊ ውድድር መክፈቻ ትልቅ ግብዓት ሲሆን፣ በዚህ የስፖርት ሁነት ላይ ከተለያዩ አህጉራት የተወጣጡ ወደ 26 የሚጠጉ የዲፕሎማት ቡድኖች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡