ብራዚል ከ ሞሮኮ ፦ የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ

You are currently viewing ብራዚል ከ ሞሮኮ ፦ የዛሬ ተጠባቂ ጨዋታ

AMN- ሰኔ 6/2018 ዓ.ም

የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ ብራዚል ከ ሞሮኮ የሚያደርጉት ግጥሚያ ይጠበቃል።

በካርሎ አንቸሎቲ የምትመራው ብራዚል ከ24 ዓመታት በኋላ ዋንጫ የማንሳት ህልሟን ለማሳካት ፤ ሞሮኮ በበኩሏ በኳታር የፃፈችውን ግማሽ ፍፃሜ የመድረስ ታሪክ ለማሻሻል ጉዞአቸውን ዛሬ ይጀምራሉ።

ብራዚል በርካቶችን ያሳመነ ብቃት ካሳየች ከርማለች። እግርኳስን የሕይወቱ አንድ አካል አድርጎ ለሚቆጥረው ሕዝቧ 24 ዓመት ያለ ዓለም ዋንጫ ማሳለፍ ከባድ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ማሸነፍ ምን ማለት እንደሆነ ማንንም ማስተማር በሚችሉ ጣልያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ቢመራም ለዋንጫ የገመተው ብዙ የለም።

የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለቤቷ ሀገር ፔሌ ፣ ጋሪናቻ ፣ ዚኮ ፣ ሮማሪዮ ፣ ሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ ፣ ሮናልዲንሆ የመሳሰሉ ስማቸው ሲጠራ የተጋጣሚ ቅዠት የሆኑ ኮከቦችን እያፈራች አይደለም።

ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ያለፈችውም በምትጠበቀው ልክ ሆና አይደለም። ብራዚል 5ኛ ደረጃ በመያዝ ነበር ተሳትፎዋን እውን ያደረገችው። ይህም ከ30 ዓመት በኋላ ያስመዘገበችው ዝቅተኛ የማጣሪያ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።

እኤአ 1994 አሜሪካ ያሰናዳችውን 15ኛ የዓለም ዋንጫ ያነሳችው ብራዚል ዘንድሮ ይህን ለመድገም እንከን የለሽ ብቃት ማሳየት ይጠበቅባታል።

ሞሮኮ በጥሩ ብቃት ላይ ትገኛለች። የአትላስ አንበሶቹ ምንም እንኳን ታሪክ ሰሪ አሰልጣኛቸው ዋሊድ ሬግራጊን አሰናብተው ሞሐመድ ኦህቢን ቢተኩም ጥንካሬያቸው አብሮ አለ። ካፍ ከሴኔጋል ነጥቆ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ያላት ሞሮኮ ትልቁ እቅዷ በኳታር የፃፈችውን ታሪክ ማሻሻል ነው።

የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በርከት ያሉ የስፖርቱ ተከታታዮች ብዙ ትኩረት ሳያገኙ ረዥም ርቀት መጓዝ ከሚችሉ ሀገራት መካከል አካተዋታል።

የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዌስሊ በጉዳት ከዓለም ዋንጫ ውጪ የሆነባት ብራዚል በዛሬው ጨዋታ ኔይማር አይደርስላትም። በሞሮኮ በኩል የትከሻ ጉዳት የገጠመው የማንችስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ኑስየር ማዝራዊ መግባቱ አልተረጋገጠም።

የዛሬው ግጥሚያ ብራዚል እና ሞሮኮ በዓለም ዋንጫ የሚያደርጉት ሁለተኛ ጨዋታ ይሆናል። ከዚህ ቀደም በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ በምድብ ጨዋታ ተገናኝተው ብራዚል 3ለ0 ማሸነፍ ችላ ነበር።

የአፍሪካ ሀገራትን ስምንት ጊዜ ገጥማ ሰባቱን ያሸነፈችው ብራዚል ፣ ብቸኛ ሽንፈቷ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የምድብ ሶስተኛ ጨዋታ በካሜሩን 1ለ0 የተረታችበት ነው።

በምድብ ሶስት የሚገኙት ሁለቱ ሀገራት ተጠባቂ ጨዋታቸውን ለሊት 7፡00 በኒው ጀርሲ በሚገኘው ሜት ላይፍ ስታዲየም ይከናውናሉ።

ዛሬ በሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች በምድብ ሁለት ኳታር ስዊዘርላንድን ምሽት 4፡00 ሰዓት ስትገጥም ፤ በምድብ ሶስት ደግሞ ስኮትላንድ ከ ሃይቲ ለሊት 10፡00 ይጫወታሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review