በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የጽንስ መቋረጥ መንስኤዎቹ፣ የተሳሳቱ አመለካከቶች እና ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች

AMN – ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

የፅንስ መቋረጥ በጥንዶች እና ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና እና የአካል ስብራትን የሚያስከትል አሳዛኝ ክስተት ነው።

የህክምና ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በአብዛኛው በእርግዝና መጀመሪያ አካባቢ ወይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሚከሰቱ የፅንስ መቋረጥ ከእናቲቱ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሚከሰቱ ናቸው።

ዋነኛው መንስኤ በፅንሱ ክሮሞዞም ወይም በዘር መል (DNA) ላይ የሚፈጠር መዛባት ሲሆን፣ ይህም ፅንሱ ሲፈጠር በሚከሰት የአጋጣሚ የሴል ክፍፍል ስህተት ምክንያት ራሱን ችሎ ማደግ ሲያቅተው በተፈጥሮ እርግዝናው የሚቋርጥበት ሂደት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በአግባቡ ቁጥጥርና ክትትል ያልተደረገባቸው እንደ ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የታይሮይድ እጢ ችግሮች እና የሰውነት መከላከያ ሥርዓት መዛባት ያሉ የእናትየው ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች ሌላው ተጠቃሽ መንስኤዎች ናቸው።

ጹንሱ በማህፀን ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርገው የፕሮጄስትሮን ሆርሞን ማነስ፣ የማህፀን በር መላላት፣ በትላልቅ የማህፀን እጢዎች ምክንያት የሚመጡ የማህፀን መዋቅር ችግሮች፣ እንዲሁም በእርግዝና ወቅት በአስቸኳይ ያልታከሙ እንደ ወባ፣ ክላሚዲያ እና ሊስቴሪያ ያሉ ከባድ ኢንፌክሽኖች ለችግሩ መከሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ብዙ እናቶች የፅንስ መቋረጥ ሲያጋጥማቸው “እኔ ባደረግኩት ስህተት የመጣ ነው” በሚል ከባድ የጥፋተኝነት ስሜትና የህሊና ወቀሳ ውስጥ ይወድቃሉ።

ሆኖም የህክምና ባለሙያዎች ይህንን አመለካከት አጥብቀው ቢቃወሙትም፤ እንደ መራመድ ያሉ ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ለእናቲቱም ሆነ ለፅንሱ እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከመጠን በላይ ከባድ ዕቃዎችን ካልተሸከሙ በቀር መደበኛ የቤትና የቢሮ ሥራዎች፣ የህክምና ባለሙያ በልዩ ሁኔታ ካልከለከለ በቀር የሚደረግ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ለፅንስ መቋረጥ ቀጥተኛ መንስኤ እንዳልሆኑ ባለሙያዎቹ ያረጋግጣሉ።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ መንስኤዎች ከተፈጥሮና ከጤና እክሎች ጋር የተያያዙ ቢሆኑም፣ እናቶች ሊያስወግዷቸው የሚገቡ እና ለፅንስ መቋረጥ ዕድልን በእጅጉ የሚጨምሩ የአኗኗር ዘይቤዎች አሉ።

ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ፣ አደገኛ እጾችን መጠቀም፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ካፌይን ማዘውተር፣ እና ለአደገኛ ኬሚካሎች፣ መርዞች ወይም ለከፍተኛ ጨረር መጋለጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ነፍሰ ጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት ከባድ ወይም መጠነኛ የደም መፍሰስ፣ የሆድ ታችኛው ክፍል ወይም የዳሌ አካባቢ ከባድ ቁርጠት፣ እንዲሁም የጀርባ ህመም እና ያልተለመደ ፈሳሽ መፍሰስ የመሰሉ አሳሳቢ ምልክቶችን ካዩ ሳይዘገዩ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የፅንስ መቋረጥ በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና ከባድ ፈተና እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ አስቸጋሪ ሂደት ውስጥ ለሚያልፉ እናቶችና አባቶች የቤተሰብ አባላት የሚያደርጉት የቅርብ ድጋፍ፣ ፍቅርና እንክብካቤ ወሳኝ ነው።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሳይኮሎጂ ባለሙያ ማማከር ስብራትን ጠግኖ ለቀጣይ ጤናማ እርግዝና ለመዘጋጀት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review