AMN – ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

በዚህ ዓመት ብቻ ከ50 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮና የመስሪያ ቦታዎች አስተዳደር ኤጀንሲ በዛሬው እለት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የመስሪያ ቦታ አስተላለፈዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት፤ እንደሀገር በትኩረት ከሚሰራባቸው የኢኮኖሚ ፒላሮች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
ይህንን ሀገራዊ ትልም ለማሳካትና ውጤታማ ለማድረግ ከተማዋም አዲስ አበባ ታምርት በሚል በርካታ ተግባራትን አከናውናለች ብለዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ በርካታ ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር እንደ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

እንዲሁም በመዲናዋ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና አምራቾች የመስሪያ ቦታን የማመቻቸት ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ ከ50 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን በማንሳት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ የመስሪያ ቦታዎችን በማልማትና ፍትሃዊ በመሆነ መንገድ በማስተላለፍ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርትን ከማሳደግም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን የሚፈጥር ነው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው የመስሪያ ቦታን የተረከቡ አምራቾች ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የመስሪያ ቦታ የተረከቡ አምራቾች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የሚያደርጋቸው ድጋፎች ወጣቶችን ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት ያሸጋገሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በራሄል አበበ