የአያቴ ልጅ ነኝ ያለቀስኩት እናቴን አስቤ ነው – ጆሲማር ጆሴ ኤቮራ ዲያስ

You are currently viewing የአያቴ ልጅ ነኝ ያለቀስኩት እናቴን አስቤ ነው – ጆሲማር ጆሴ ኤቮራ ዲያስ

AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

“ቮዚንሃ” በሚለው የቅጽል ስሙ የሚታወቀውና ዕድሜው 40 የሞላው የኬፕ ቨርዴው አንጋፋ ግብ ጠባቂ ጆሲማር ጆሴ ኤቮራ ዲያስ፣ በዓለም ዋንጫ መድረክ ሀገሩ ከኃያሏ ስፔን ጋር 0 ለ 0 አቻ እንድትለያይ ተዓምራዊ ብቃት በማሳየት የጨዋታው ኮኮብ መሆን ችሏል።

ነገር ግን ጨዋታው ሲጠናቀቅ መላው ቡድን በደስታ ሲያከብር ፣ እሱ ግን በስታዲየሙ መሃል ተንበርክኮ በከፍተኛ ስሜት ማልቀስ ጀመረ።

ይህ እንባው ተራ የደስታ መግለጫ ሳይሆን ፣ በውስጡ ትልቅ የናፍቆትና የሕይወት ውጣ ውረድ ታሪክ ያዘለ ነበር።

ቮዚንሃ በሕፃንነቱ አባቱ በውትድርና፣ እናቱ ደግሞ ለኑሮ ሌት ተቀን በመልፋቷ ምክንያት በአያቶቹ ፍቅርና እንክብካቤ ነው ያደገው።

ያሳዩትን ውለታ ለመዘከርም “ትንሿ አያት” የሚል ትርጉም ያለውን “ቮዚንሃ” የሚለውን ስም በማልያው ላይ አትሞ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ውስጥ መራራ የሕይወት ልምድን አሳልፏል።

ይህንን ታሪካዊ ቀኑን እንዲያዩለት ይመኝ የነበሩት አያቶቹ ከዓመታት በፊት በመሞታቸውና ስኬቱን በአካል ሊያካፍላቸው ባለመቻሉ በትልቁ መድረክ ላይ የሃዘን ስሜት ፈጥሮበታል።

ከሁሉ በላይ የዓለምን ሕሊና የገረመውና ያስለቀሰው ግን እናቱን አስቦ ነበር ፤ በትልቁ መድረክ ሀገሩን ሲያስጠራ እናቱ ስታዲየም ተገኝታ እንድታየው ቢፈልግም፣ የቪዛ ክፍያ ገንዘብ ባለመኖሩ ምክንያት ሳትመጣ ቀርታለች።

በቢሊዮን ዶላር በሚንቀሳቀስበት የስፖርት ዓለም ውስጥ በአንዲት እናትና ልጅ ፍቅር መካከል የገንዘብ እጥረት ያስከተለው እውነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ የነካ ሲሆን፣ በዚህም በአንድ ምሽት የኢንስታግራም ተከታዮቹ ወደ አምስት ሚሊዮን አድጓል።

የቮዚንሃ ታሪክ የሰው ልጅ ምንም ያህል ዝነኛ ቢሆን፣ የሕይወቱ መሠረት የሆኑትን እናትና አያቶቹን ማሰብ የነፍስ ትልቁ ሀብት መሆኑን ያሳየ ሕያው ምስክርነት ሆኖ አልፏል ። “እግር ኳስ ከስፖርት በላይ” የሚባለውም ለዚህ ነው ።

በቢንያም ከድር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review