አዲስ አበባ፡ ለአፍሪካ ሕፃናት የልህቀትና የተሞክሮ ማዕከል እየሆነች ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባ፡ ለአፍሪካ ሕፃናት የልህቀትና የተሞክሮ ማዕከል እየሆነች ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ፡ ለአፍሪካ ሕፃናት የልህቀትና የተሞክሮ ማዕከል እየሆነች ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የመጀመሪያው ዓለም-አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳስታወቁት፣ አዲስ አበባን ለአፍሪካ ሕፃናት ምርጧ ከተማ ለማድረግ የተያዘው ግብ በተጨባጭ ውጤት እየታጀበ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በ2015 ዓ.ም 11 ብቻ የነበሩት የሕፃናት ማቆያዎች ዛሬ 1 ሺህ 100 መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች በቁጥር 20 ከነበሩበት ወደ 5 ሺህ ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ 1.3 ሚሊየን ሕፃናት ተገቢ የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙም ዘርፈ ብዙ መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።

ለሕፃናት የምትመች ከተማ ለሁሉም ትመቻለች ያሉት ከንቲባዋ፣ ከተማዋን ለነገዎቹ ተረካቢዎች ምቹ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ይህ የልጆቻቸውን ደህንነት ተጠብቆ ስራ ለመዋል ለሚቸገሩ እና አቅመ ደካማ ለሆኑ 330 ሺህ ቤተሰቦች መልካም ዜና ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ መንግስት በቀዳማይ ልጅነት ልማት ላይ ባደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት ነፃ የምግብ፣ የህክምና እና የእንክብካቤ አገልግሎት እያገኙ ነው ብለዋል፡፡

ከ5 ሺህ በላይ ባለሙያዎች ወላጆችን በቤት ለቤት ምክር እያገዙ እንደሚገኙ በመጥቀስም፣ በትምህርት ዝግጁነት ረገድ የታየው ውጤት ከ49 በመቶ ወደ 90 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review